ጥቅምት ፳፯ ተዝካረ ስቅለቱ ለእግዚእነ

በኩረ ፍሥሐ ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ጥቅምት ፳፯ ተዝካረ ስቅለቱ ለእግዚእነ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

እንኳን ለመድኃኔዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል ዝክረ ጥንተ ስቅለት አደረሳችሁ አደረሰን

ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ “ ከመዝ ነአምን ዘአልቦቱ እም በሰማያት፤ ወአብ በዲበ ምድር ” በሰማይ ያለእናት ከአብ መወለዱን፣ በምድርም ያለ አባት ከድንግል ማርያም መወለዱን እናምናለን። ይህንንም አባቶቻችን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት፣ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል ፤ ድኀረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት፣ መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ የተወለደ፤ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትስብእቱ ብለው አምልተው እንዲያስተምሩን  “ከመ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ” ትርጉሙም  እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው ማለት ነው።  ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ፴፭፥፳፩

 

መጋቢት ፳፯  በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  የተሠቀለበት ጥንተ ስቅለቱ የሚታሰብበት ቀን ነው ፡፡  ይሁን እንጂ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በዲሜጥሮስ ቀመር መሠረት አጽዋማትን በጠበቀ መልኩ ከትንሣኤ በዓል በፊት ያለውን አርብ “ስቅለት” ተብሎ እንዲከበር ሥርአት ሠርተዋል፡፡መጋቢት ፳፯ ቀን በዓቢይ ጾም ስለሚውል በዓቢይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት ፳፯ ተዛውሮ ደስ ብሎን እንድናከብረው ቤተክርስቲያን ሥርዓት ሰርታለች ።

 

ጥቅምት ፳፯ ዝክረ ጥንተ ስቅለቱን ቤተክርስቲያናችን ጌታችን በመስቀሉ ስለፈጸመልን የማዳን ስራ “ በመስቀሉ ወበቃሉ አዕበዮሙ ለአበዊነ ” ። በመስቀሉና በቃሉ አባቶቻችንን ከፍ ከፍ አደረጋቸው እያለች እየዘመረች ታስበዋለች። ከዚህም በተጨማሪ ጥቅምት ፳፯  በወርኀ ጽጌ ውስጥ ያለ በመሆኑ “  …እስመ ውእቱ ክብሮሙ ለቅዱሳን መድኃኒቶሙ ለጻድቃን  አሠርገዋ ለምድር በጽጌ ሮማን ስብሐተ ዋህድ ዘምስለ ምህረት በመስቀሉ ወበቃሉ አዕበዮሙ ለአበዊነ ” እያለች የቅዱሳን ክብራቸው የጻድቃን መድኃኒት የሆነው ጌታ ምድርን በአበባ የሚያስጌጣት እንደሆነ በመመስከር ትዘምራለች ።

“እስመ አንተ ትክል አንጽሖትየ እግዚኦ  ወበቃልከ እለ ለምፅ አንጻሕከ  ወበጽጌያት ምድረ አሠርጐከ  ወበመስቀልከ ለጻድቃን አብራህከ ”  ልታነጻኝ ይቻልሃል አቤቱ ለምጻሞቹን በቃልህ እንጽተሃልና እያሉ አባቶቻችን በመስቀሉ ለጻድቃን ማብራቱን እያሰቡ በዓሉን በመዝሙር በደስታ ያከብሩታል

 

ወበከመ ሙሴ ሰቀሎ ለአርዌ ምድር በገዳም ከማሁ ሀለዎ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው ይሰቀል” ዮሐ ፫፥፲፬ ሙሴ እባብ በምድረ በዳ እንደሰቀለ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው  ብሎ እንደተናገረ  የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ድኅነት የተሰቀለው መጋቢት ፳፯ ቀን ነው ።

 

ክርስቶስ ስለስቅለቱ ሲናገር ምሳሌ የሚሆነውን፣ ሙሴ በምድረ ባዳ የሰቀለውን፣ የነሐሱን እባብ “ሙሴ እባብ በምድረ በዳ እንደሰቀለ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው” ብሎ ምሳሌውን ተናግሯል።

 

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እስራኤልን ከደመና መና አውርዶ፣ከጭንጫ ውሀ አፍልቆ ቢመግባቸው ከዚህ ምድሩ ብቅ፣ሰማዩ ዝቅ ቢልለት፣ ከደጋ ላይ ቢሆንለት የውርጭ ሰደቃ እያበጀ፣ ውሀውን እያረጋ፣ መና መገብኳችሁ ይላል እንጅ ይክልኑ እግዚአብሔር ሠሪዓ ማዕድ በገዳም። ቆላ በሆነማ ባልተቻለውም ነበር ብለዋል ።ጌታም ሊያስተምራቸው ፣  የርሱን ከሃሊነት ሊያሳያቸው፣  የእነርሱንም ሀሰት ሊገልጥባቸው ፣  ሙሴን ነቅዓ ማይ የሌለበት በርሐ ይዘሀቸው ውረድ ብሎት ቢሄዱ መናው ወርዶላቸዋል፣ ውሀውም ፈልቆላቸዋል ።ነገር ግን ነዘር የሚባል እባብ እየነከሰ ይፈጃቸው ጀመር።ከዚህ በኋላ እስራኤል ሙሴ ዘንድ ሂደው ከጌታ ምህረት ቸርነት ከሰው ስሕተት ኃጢአት አይታጣም በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ተናግረን በድለናል  እባቦችን ከኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር አመልክትልን አማልደን አሉት።ሙሴም ስለሕዝቡ  ወደ እግዚአብሔር ቢጸልይ  ጽሩዩን ብርት አርዌ አስመስለህ ሠርተህ ከሚገናኙበት አደባባይ ከእንጨት ላይ ስቀልላቸው አለው። ሙሴም እባብን ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የነሐሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። (ኦሪ ዘኁ ፳፩ ፥፩፡፱)

 

ይህንም ምሳሌ አባቶቻችን በትርጓሜ ወንጌል ቅዱስ እንዳስቀመጡልን አርዌ ምድር የዲያብሎስ፤አርዌ ብርት የጌታ ምሳሌ ነው ። በአርዌ ምድር(እባብ) መርዝ እንዳለበት በዲያብሎስም ፍዳ ኃጢአት አለበት።በአርዌ ብርት መርዝ እንደሌለበት በጌታም ፍዳ ኃጢአት የለበትም ።አርዌ ብርት በአርዌ ምድር አምሳል መሰቀሉ ጌታ በአምሳለ እኩያን እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ ለመሰቀሉ ምሳሌ ነው። ዳግመኛም  “ተኈለቈ ምስለ ጊጉያን” ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሯልና  ኢሳ  ፶፫፥፲፪  የሚለውን ትንቢት ፈጽሟል። ምሳሌውን አውቆ አስመስሏል ትንቢቱንም አውቆ አናግሯል ።

 

ጲላጦስ አይሁድን ከሁለቱ ማናቸውን ላድንላችሁ ትወዳላችሁ ቢላቸው በርባንን ፍታልን ክርስቶስ የተባለ ኢየሱስን ግን ስቀለው አሉ ።ጲላጦስም  በዚህ ሰው ደም ከመጣ ፍዳ ሁሉ ንጹሕ ነኝ ብሎ ባደባባይ እጁን ታጠበ። አይሁድ ደሙ በኛም በልጅ ልጆቻችንም ይሁን አሉ። እርሱም በርባንን ፈታላቸው ጌታንም አሳልፎ ሰጣቸው። ማቴ ፳፯ ፥፳፭

 

ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ “ሊቃነ መላእክት በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአደባባይ አቆሙት፤ ኃጢያትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፤ በመኳንንት በሚፈርደው በርሱ ፈረዱበት” ፡፡  እንዲል ክርስቶስን አይሁድ ስቀለው ብለው ፈረዱበት

 

አክሊልን የሚያቀናጀውን የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን አነገስንህ ብለውታልና ጭፍሮች በፍና ተሣልቆ የእሾህ አክሊል ታተው ደፉለት “ወጸፈሩ ሐራ አክሊለ ዘሦክ ወአስተቀጸልዎ ዲበ ርእሱ” ዮሐ ፲፱፥፪ ። ኢየሱስ ክርስቶስ  የእሾኽ አክሊል በመቀዳጀቱ ዕፀ በለስን በልቶ  “ምድር እሾኽንና አሜከላን ታበቅልብኻለች” ዘፍ  ፫፥፲፰  ብሎ የፈረደበትን አዳም  ስለርሱ ክሶ መርገሙን ደምስሶለታል ።

 

መጋቢት ፳፯ ቀን ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ፤ የተሰቀለው የክብር ባለቤት ሰማይን የፈጠረ ነውና  ፀሐይ ጨልማለች፣ ጨረቃ ደም ሆኗል፣ ከዋክብት ረግፈዋል። የተሰቀለው የክብር ባለቤት ምድርንም የፈጠረ ነውና በምድር የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለኹለት ተቀዷል፤ ምድር ተናውጣ ዐለቶች ተሠንጥቀዋል፤ መቃብራት ተከፍተዋል፤ ከ፭፻ በላይ ሙታን ተነሥተዋል (ማቴ ፳፯ )፡፡

 

ኦ አእዳው እለ ለሐኳሁ ለአዳም ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ፤ ኦ አእጋር እለ አንሶሰዋ ውስተ ገነት ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል

አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ፤በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ፡፡ እንዲል  ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ ስቅለቱን በዲሜጥሮስ ቀመር አውጥተን የጌታን መከራውን አስበን በስግደት ህማማቱን እናስባለን በዝክረ ጥንተ ስቅለቱ በጥቅምት ፳፯ ደግሞ በመስቀል የተደረገልንን አስበን እናመሰግነዋለን፡፡

 

ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት መታሰቢያ ጋር  ቤተ ክርስቲያን በ15ኛው መ.ክ.ዘ  የነበሩትን አቡነ መብዓ ጽዮንን ታስባለች፡፡  አቡነ መብዓ ጽዮንን  አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን  ‹‹ በዕለተ ዓርብ የተቀበልከውን  መከራ ግለጽልኝ ››ብለው በጸለዩ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ የተቀበላቸውን መከራዎች ሁሉ አሳያቸው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ከርስቶስን መከራ ካዩበት ቀን ጀምሮ ሕማሙን መከራውን ግርፋቱን እስራቱንበጠቅላላ አስራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል በማሰብ ጀርባቸውን በአለንጋ ይገርፉ ፤ ራሳቸውን በዘንግ ይመቱ ነበር፡፡  የጌታችንን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ዘወትር ስለሚያለቅሱ  ዐይናቸው ጠፍቶ ነበር፡፡ ነገር ግን እመቤታችንቅድስት ድንግል ማርያም  የብርሃን ጽዋ ይዛ መጥታ ዐይናቸውን ቀብታ አድናቸዋለች፡፡ በዚህ የተነሳ ‹‹በትረ ማርያም›› እየተባሉ እንደሚጠሩ ገድላቸው ያስረዳል፡፡ በዚህ መሰረት ጥቅምት ፳፯ ቀን ለአቡነ መብዓ ጽዮን ቃልኪዳን የገባበት ቀን በመሆኑ በየዓመቱ ጥቅምት ፳፯  ቀን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዝክረ ጥንተ  ስቅለቱ ጋር ይከበራል፡፡ የጻድቁ አቡነ መብዓ ጽዮን በረከትና ረድኤት ይደርብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር