ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤው ስኬታማ እንደነበር ተገለጸ፡፡

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ  ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤው ስኬታማ እንደነበር ተገለጸ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓና  የአሜሪካ ማዕከላት አስተባባሪነት ከጥቅምት ፲-፲፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም/October 20-21/2018  በሰሜን አሜሪካ  አትላንታ  ጆርጂያ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍና የብራና ቅርሶች በኢትዮጵያ በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው  ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ  ስኬታማ እንደነበር  የኮሚቴው  ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ  ገለጹ፡፡

ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ጉባኤው  መጠናቀቁን  አስመልክተው ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር   በሁለቱ ቀናት ጉባኤ ከአውሮፓ፣ከኢትዮጵያ፣ ከአሜሪካ  የተለያዩ  ክፍለ ግዛቶች በመጡ ኢትዮጵያውያንና  የውጭ ተመራማሪዎች 3 ቁልፍ  ንግግሮችና 13 ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕ/ር  ስቲፍ  ዴልማተርና  ሊቀ ካህናት  ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ  “ቁልፍ  ተናጋሪ“ በመሆን ጥናቶቻቸን  ያቀረቡ ሲሆን   የብራና መጻሕፍትና የግዕዝ ሥነ ጽሑፍን  መሰረት ያደረጉ የሃይማኖት፣የታሪክ፣የዜማ፣የቋንቋና ባሕል፣ የመድኃኒት፣ የትርጓሜ፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣የብራና አዘገጃጀትን የተመለከቱ ጥናቶች በተመራማሪዎቹ  ቀርቦ ውይይት ተደረጓል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች፤ በእለቱ ጉባኤውን በጸሎት የከፈቱትና ቃለ ምዕዳን የሰጡት ብፁዕ አቡነ ሰላማ በሰሜን አሜሪካ የፍሎሪዳና  ኦሀዮ ሀገረ ስበከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ የአትላንታ  ጆርጅያ  ከተማ  ምእመናን (የማኅበረ ቅዱሳን አባላት)፣ የደብር አለቆች፣ የውጭ ዜጎች (ጃማይካውንን ጨምሮ)  መሆናቸውን  ገልጸዋል፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ዓለም አቀፍ  የጥናት ጉባኤው በመቅረቡ ደሰተኛ መሆናቸውን ገልጸው በጉባኤው ያልተሳተፉ ሰዎች ብዙ ምስጢር እንዳመለጣቸው ገልጸዋል፡፡

ጥቁር አሜሪካዊቷ  ዶ/ር ጌይ  ባይረን  ጥናታቸውን  ሲያቀርቡ  እንደገለጹት “ የኢትዮጰያ  ቤተክርስቲያን ባለውለታችን ናት::  የብራና መጻሕፍቱ በተለያየ ዓለም መገኘታቸው የቀደሙ አባቶች እውቀትና ተጋት ከፍተኛ እንደነበር ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተሰፋችን ናት፡፡ ኢትዮጵያን አይቻለሁ፡፡  ደብረ ሊባኖስ ገዳምም ደርሻለሁ፡፡ የአብነት ተማሪዎች ሲማሩ  ተመልክተን ደስ ብሎናል፡፡  ባለፈው ሁለት ዓመታት የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ብራና መጽሐፍ አስመልሰናል፡፡ ወደፊትም  ከእናንተ ጋር ብዙ ለመስራት አሰባለሁ፡፡“  ብለዋል፡፡

ሊቀ ካህናት  ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ በጉባኤው መዝጊያ ወቅት ሲገልጹ ”ዛሬ ተሰፋዬን አለመለማችሁት  አምላኬን አመሰግናለሁ ፡፡ ሁሉ እያላት ደሃ ለሆነችና ጠበቃ  ላጣች  ቤተክርስቲያን  ጠበቃ ሁኗት ፡፡ “ በማለት የጉባኤውን ተሳታፊዎች አደራ በማለት በጸሎት ዘግተዋል፡፡

ሦስተኛው  ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጥናት ጉባኤ የትና መቼ እንደሚሆን ኮሚቴው የሚገለጽ ሲሆን በርካታ ተመራማሪዎች ሊሳተፉበት ይችላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡