በድንግልናሃ ንጹሕ እግዚአብሔር ተወልደ

በድንግልናሃ ንጹሕ እግዚአብሔር ተወልደ

                                ቀሲስ ሳሙኤል ተስፋዬ

በፈቃደ አቡሁ ወረደ፣ኀበ ማርያም ተአንገደ፤ በድንግልናሃ ንጹሕ እግዚአብሔር ተወልደ። በጎለ እንስሳ ተወድየ፣ አምኃ ንግሡ ተወፈየ፤ ወከመ ሕጻናት በከየ፣ እንዘ ይስእል እምአጥባተ እሙ ሲሳየ።

በአባቱ ፈቃድ ወረደ፣ በማርያም ዘንድ፣ እንግዳ ሆነ፣ እግዚአብሔር በንጹሕ ድንግልናዋ ተወለደ። በእንስሳት በረት ተጨመረ፣ የንግሡንም እጅ መንሻ፡ ተቀበለ፣ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕጻናት አለቀሰ። (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ)

 

እግዚአብሔር አምላክ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ፈጠረ ሌሎች ፍጥረታት ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጠሩ ሰውና መላእክት ግን ፍቅሩን ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ተፈጠሩ፡፡ ዘፍ 1፡1

የሰው ልጅን /አዳምን/ ፈጥሮ የሚያስፈልገውን አዘጋጅቶ፣ ዕውቀትንና ሥልጣን ሰጥቶ፣ በጸጋ አምላክነትን ሾሞ ፣መመሪያ ሰጥቶ፣ በክበር እንዲኖር ፈቀደለት ፡፡ በመጀመሪያው ዕለትና ሰዓት ከተፈጠሩት መላእክት መካከል በክብር ይልቅ የነበረው ሳጥናኤል /የኋላ ስሙ ዲያብሎስ /አምላክነት መሻቱ ተወርዶ ሳለ አዳምንም በተዋረደበት ምኞትና ፍላጎት እንዲወድቅ ክብሩን እንዲያጣ ከአምላኩም እንዲለይ አደረገው፤ እግዚአብሔርን፣ ጸጋውን፣ ሹመቱን፣ አጣ /ኃጥአ/፡፡ ኃጢአት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከዚህ የተወሰደ ነው፡፡

 

አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱና ክብሩን በማጣቱ ተጸጽቶ ንሰሐ ገባ ፡፡ ሥርየተ ኃጢአት የሚሆን መስዋእትም በማቅረቡ፤ እግዚአብሔር አምላክ ልመናውንና መስዋእቱን ተቀብሎ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ቃል ኪዳን ገባለት መዓልትንና ዓመታትን በዚህ ምድር ላይ ሠራሁልህ፡፡ ይኸውም እነርሱ እስኪፈጸሙ ድረስ በምድር ላይ ትኖርና ትመላለስ ዘንድ ነው፡፡ የፈጠረችህና የተላለፍካት ከገነት ያወጣችህና በወደቅህም ጊዜ ያነሳችህ ዳግመኛም አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም የምታድንህ ቃሌን እልክልሃለሁ” /ገድለ አዳም/ ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም ነገረው፡፡ አዳምም አምስት ቀን ተኩል የሚለውን ቃል ከእግዚአብሔር በሰማ ጊዜ የእነዚህን ታላላቅ ነገሮች ትርጓሜ ሊያስተውል አልቻለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምስት ቀን ተኩል ማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት መሆናቸውን ገልጾ አርአያውና አምሳያው ለሆነው አዳም በቸርነቱ ተርጎመለት፡፡ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ተስፋ ሰጠው፡፡ ዘፍ 2፡7 ፣ሔኖክ 19 ፡19 ፣ ኩፋሌ 5፡6

 

አዳምም ይህንን ተስፋ ለልጆቹ አስተማራቸው፤ ልጆቹም ተስፋው የሚፈጸምበትን ጊዜ ለማወቅ በፀሐይ፣ በጨረቃና በክዋክብት ዘመናትን እየቆጠሩ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ” ያለውን የአዳኝ ጌታ መወለድን ነብያት ትንቢት እየተናገሩ፤ አበውም ሱባኤ እየገቡ ተስፋውን ይጠብቁ ነበር፡፡ ከነሱም ውስጥ:-

  1. ሱባኤ ሔኖክ

ሔኖክ ሱባኤውን ሲቆጥር የነበረው በአበው ትውልድ ሲሆን ሰባቱን መቶ ዓመት አንድ እያለ ቆጥሯል። በስምንተኛው ሱባኤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናግሯል። አቆጣጠሩም ከአዳም ጀምሮ ነው። 8×700=5600ዓመት ይሆናል። 5500ዓመተ ዓለም ሲፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደ ያጠይቃል። ትንቢቱም እንዲህ ይላል። “ስምንተኛይቱ ሰንበት ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅባት ሰባኤ ናት፡፡ ሰይፍም ለርሰዋ ይሰጣታል፤ ታላቁ ንጉሥ የሚመሰገንበት ቤትም በርሰዋ ይሰራል፡፡ ምሥጋናውም ዘላለማዊ ነው፡፡” ሔኖክ 35፡ 1-2 ክፍል 91 በማለት ሲተነብይ መተርጉማን እንዲህ ይመልሱታል፡፡ ለርሰዋ ሰይፍ ይሰጣታል ማለቱ፤ ጸድቅና ኩነኔ የሚታወቅበት ወንጌል ያን ጊዜ በዓለም ሁሉ ትሰበካለች ማለት ነው፡፡ የታላቁን ንጉሥ ቤት ይሠራል ማለቱ፤ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቱስ የሚመሰገንበት ቤተክርስቲያን ትሰራለች ማለት ነው፡፡ ምስጋናውም ዘላለማዊ ነው ማለቱ፤ ሰውና መላእክት በአንድነት ሆነው “ሰብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” እያሉ ዘወትር ያመሰግናሉ ማለት ሲሆን ስምንተኛይቱ ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠችበትን ዕለት ልደት ክርስቶስ ናት ይሏታል፡፡

2. ሱባኤ ዳንኤል

ስለ ጌታችን ሰው መሆን ጊዜ ወስኖ ሱባኤ ቆጥሮ የተናገረው ዳንኤል ነው፡፡ የዳንኤል ሱባኤ የሚቆጠረው በዓመት ነው ፡፡ ዳንኤል 70ው ዘመን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ ተብሎ በኤርምያስ የተገረውን ትንቢት እያስታወስ ሲጸልይ መልአኩ ቅ/ገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጾ እንዲህ ብሎታል፡፡ “እግዚአብሔር ልምናህን ሰምቶሃልና እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ አሁንም ነገሩን መርምር ራእዩንም አስተዋሉ ኅጢአት የሚሰረይበትን ቅዱሰ ቅዱሳን ጌታም የባህርይ ክብሩን ገንዘብ የሚያደርግበት ሰባው ሱባኤ ሊደርስ ሊፈጸም ነው ብለህ ወገኖችህን ቅጠራቸው ብሎታል፡፡” /ዳን 9፡22- 25 ኤር 29፡1ዐ/

ሰባ ሱባኤ አራት መቶ ዘጠና ዓመት ነው /7ዐX7= 490/ ይህ ጊዜ ከሚጠት እስከ ክርስቶስ መምጣት ያለው ጊዜ ነው /ትርጓሜ ሕዝ፡4፡6/

  1. ሱባኤ ኤርምያስ

ኤርምያስ ከባቢሎን እንደተመለሰ በፈረሰው ቤተ መቅደስ ውሰጥ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ራዕይ አየ በሦስተኛው ቀንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ “ፈጣሪያችንን በአንድ ቃሉ አመሰግኑ የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አመስግኑ ከዚህ በኋላ ሰው ሊሆን ሥጋ ሊለብስ ወደዚህ ዓለም ሊመጣ የቀረው 333 ሱባኤ ዕለት ነውና እርሱ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፡፡ አሥራ ሁለት ሐዋርያትንም ይመርጣል…፡፡” ተረፈ ኤር 11፤37 ፣38፣42-48፡፡ ኤርምያስ ሱባኤውን የጀመረበትን ትንቢቱን የተናገረበት ራእዩን ያየበት ዘመን ዓለም በተፈጠረ 5054 ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ ከተነገረበት እስከ ክርስቶስ ልደት ያለው ጊዜ 446 ዓመት ነው፡፡

ይኸውም በኤርምያስ ሱባኤ አንዱ 49ዐ ዕለት ነው መላው ሱባኤ 49ዐX333 = 163,170 ዕለት ሲሆን ወደ ዓመት ሲለወጥ 163, 170÷365 =446 ዓመት

ኤርምያስ ሱባኤውን መቁጥር የጀመረበት ዘመን …….. 5ዐ54 ዓመተ ዓለም

ትንቢቱ ከተነገረበት ዓመት እስከ ክርስቶስ ልደት ……. 446 ዓመት

በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት 55ዐዐ ዓመት ሲፈጸም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቱስ መወለዱ በዚህ ይታወቃል፡፡

  1. ዓመተ ዓለም

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምረው ሱባኤያትንና ሰንበታትን አውቀው ከአዳም እስከ ክርስቶስ ያለውን ዘመን ቁጥር 55ዐዐ ዓመት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ይኸውም

ከአዳም አስከ ኖኅ            2256 ዓመት

ከኖኅ እስክ ሙሴ            1588 ዓመት

ከሙሴ እስከ ሰሎሞን        593 ዓመት

ከሰሎሞን አስከ ክርስቶስ   1063 ዓመት

55ዐዐ ዓመት

ጌታችን ኢየሱስ በተነገረው ትንቢት፤ በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት /ዓመተ ዓለም፣ ዓመተ ኩነኔ ፣ዓመተ ፍዳ/ አምስት ቀን ተኩል / 55ዐዐ ዓመት/ ሲፈጸም /በእግዚአሔር ዘንድ 1ዐዐዐ ቀን እንደ አንድ ቀን ናት፡፡ 2ኛ ጴጥ. 3፤8 / በ5501 ዓመት ማክሰኞ ታኀሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡

 

“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ሥምረቱ ለሰብእ” አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘመኑ ፍጻሜ /የገባው ቃል ኪዳን፣ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባዔ/ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ያጣነውን ልጅነት ሊመልስልን፣ ከተቀማነው ርስት ሊያስገባን፣ የገባንበትን እዳ ሊከፍልልን ተወለደ፡፡

የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ ፡፡ ገላ 4፣4 እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ቅዱስ ኤፍሬምም “ ቅድስት ድንግል ማርያም ፍጥረታትን ያስገኘ፤ የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችልን፡፡ የአሮን በትር ለምልማና ፍሬ አፍርታ ተገኝታ ነበር፤ ይህም ክርስቶስ በድንግልና የመወለዱ ምሳሌ ነው፡፡ እጹብ ድንቅ የሆነ ልደት በዛሬዋ ቀን እውን ሆነ፡፡ ድንግል የሆነችው ቅድስት ማርያም በድንግልና ጌታችንን መድኃኒታችንን ወለደችልን፡፡” ብሏል፡፡

“የእሥራኤል እረኛ ሆይ አድምጥ … በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ” ብሎ የለመነዉ የዳዊት ልመና በእዉነት ተፈጸመ፡፡ መዝ 70፥1። የእስራኤል እረኛ፤ በእረኞች መካከል በከብቶች በረት ተወለደ። ሉቃ 2፥7፡፡ እረኞች ለእረኛቸው ዘመሩ፤ ላሞች፣ በጎችና አህዮች በበረት የተኛውን ሕፃን በትንፋሻቸው አሟሟቁ። በኦሪት ድንኳን በሙሴ ሕግ መሠረት ለመሥዋዕት ይቀርቡ የነበሩ እንስሳት በልደቱ ደስ ተሰኙ፤ የነርሱን መሥዋዕት የሚያስቀር አማናዊው የእግዚአብሔር በግ ተወልዷልና።

ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እግዚአብሔር በጨለማው ዓለማችን ተወለደ። (ዮሐ.1፥9-14) ነቢያትና መምህራን ጠፍተውባት፣ የኃጢአት ጨለማ ዉጧት፣ በድንቁርና ባሕር ውስጥ ሰጥማ በነበረችው የሰው ልጆች ዓለም የእውነት ፀሐይ ወጣ። እነሆ ይህን ይገልጥ ዘንድ መድኅን በእኩለ ሌሊት በጨለማ ተወለደ፤ በተወለደ ጊዜ ግን ክብሩ በዙርያው አበራ። (ሉቃ.2፥8-9)

ለመንግሥቱ ወርቅ ተገበረለት። ኃያል መንግሥቱን ግን በምድር ላይ በትህትና ነበር የገለጣት፤ በከብቶች በረት በመወለድና በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ በመሄድ። (ሉቃ.19፥28-38) የአባታችን የዳዊት መንግሥት ያለልክ ከፍ ከፍ አለች፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ የዳዊት ልጅ ሆኗልና። ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ “እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል ልጅም ይባላል፤ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለዉም” ብሎ የተናገረዉ ዛሬ ተፈጸመ፡፡ (ሉቃ.1፥32)፡፡

 

በባሕርይው የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነዉ የእግዚአብሔር ልጅ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ነስቶ ሰዉ በሆነ ጊዜ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን እስከ ጽርሐ አርያም ድረስ ከፍ ከፍ አደረጋት። እነሆ ንጉሥ ክርስቶስ በያዕቆብ ቤት (በምእመናን) ላይ ለዘላለም ነገሠ። ለመንግሥቱ የአሕዛብ ነገሥታት ተገዙላት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና ፍጥረታት ሁሉ ይገዙላታል። (ኤር.23፥5)

ለክህነቱ ዕጣን ተሰጠው። ክህነቱም የአበውን እና የሌዋውያንን ክህነት የምትፈጽም የዘላለም ሰማያዊት ሥራው ናት። እነሆ የአብ ሊቀ ካህናት እርሱ የሰውን ባሕርይ ከራሱ ጋር አስማማ። ራሱ ካህን፣ ራሱ መሥዋዕት፣ ራሱ ተቀባይ ሆኖ የፈጸማት የክህነት ሥራው የዘላለም ድኅነትን አስገኘች።

ለሞቱ ከርቤ ቀረበለት። እነሆ እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት በሞቱ ሞትን ድል ለመንሣት ነውና በልደቱ ሞቱ ተሰበከ። ከርቤ ለሞቱ ሲቀርብለት የማይሞተው እርሱ ለሰው ልጆች ሲል የሚሞት ሥጋን እንደለበሰ ታወቀ።

የአሕዛብ ነገሥታት ወርቅ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ጽሩይ፣ ንጹሕ፣ ሰማያዊ የሆነ ልቦናን እና እምነትን ለእርሱ እናቀርባለን። (1ኛ ጴጥ.1፥6) ሰብአ ሰገል ራሱ የፈጠረውን ወርቅ ገበሩለት፤ እኛም በርሱ ጸጋና ሥራ ያገኘነውን ንጹሕና ሰማያዊ እምነታችንን እናቀርብለታለን (ይሁ.3)።

ነገሥታቱ ዕጣን ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ቂም በቀል የሌለበትን፣ ከመልካም እና ከንጹሕ ልብ የሚወጣ የምስጋና ጸሎት እናቀርባለን፤ “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴንም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።” እንዳለ ንጉሥ ዳዊት (መዝ.140፥2) ።

ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል ለሚቀበለው ሞት ከርቤ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለሰው ልጆች ያለንን ፍቅር ለእርሱ እናቀርባለን። ነገሥታቱ እርሱ ከፈጠረው ከርቤ ወስደው እጅ መንሻ አቀረቡ፡፡ ምእመናን ደግሞ ከእርሱ ከተማርነው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከተቀበልነው ፍቅር መልሰን ለእርሱ እናቀርባለን። “እርሱ ስለኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል፡፡ (1ኛ ዮሐ.3፥16)።”

ነቢዩ ኢሳይያስ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸዉ” ብሎ የተናገረዉ ትንቢት ተፈጸመ (ኢሳ.9፥2)። የቅድስናዉ ተራራና ማደሪያው ወደ ሆነች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይወስደናል፡፡ በዚች የዘላለም ሃገራችንም የሚያበራልን ፀሐያችን እርሱ ነዉ፡፡ (ራእይ.21፥23)።

እነሆ ሰው የመሆኑ ዜና የሰው ልጆች ሁሉ ደስታ ነው፡፡ “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” የሚል ዜና በሰማያውያን መላእክት ተሰበከ። (ለቃ.2፥11)

የምድር ኃያላን ነገሥታት በከብቶች በረት ውስጥ በጨርቅ ተጠቅልሎ ለተኛው ሕፃን መብዓ አቀረቡ። ንጹሐንና ኃያላን የሚሆኑ የሰማይ መላእክት ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ፍቅር ሲል እንደ ሕፃን ተጠቅልሎ ሲያዩ በታላቅ ትሕትና ከእረኞች ጋር ዘመሩ። (ሉቃ.2፥13)

በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ድንቅ ነገር ተደረገ። ዳዊት በወርቅ ያጌጠ የተልባ እግር መጎናጸፊያ የለበሰባት ቤተልሔም የሰማይና የምድር ፈጣሪ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተገኘባት። ቤተልሔም ከዳዊት ዘመን አብልጣ ከበረች፤ የእግዚአብሔር ክብር አብርቶባታልና፤ የልዑላን መላእክት ዝማሬ ተሰምቶባታልና። (ሚክ.5፥2)

 

በዚህች ዕለት እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኞች መጣ፤ ስለዚህ ጻድቁ በኃጢአተኞች ላይ አይታበይ፡፡ በዚህች ቀን የሁሉ ጌታ የሆነው እርሱ ወደ ባሮቹ መጣ፤ እናንተ ጌቶች ሆይ እንደ ጌታችን ለአገልጋዮቻችሁ ቸርነትን አድርጉላቸው፡፡ በዚህች ቀን ባለጠጋ የሆነው እርሱ ስለ እኛ ሲል ደሃ ሆነ፡፡ እናንተ ባለጠጎች ሆይ ከማዕዳችሁ ለድሃው አካፍሉ፡፡ በዚህች ቀን እኛ ያላሰብነውን ስጦታ ከጌታ ዘንድ ተቀበልን፤ እኛም ምጽዋትን ለሚጠይቁን ድሆች ቸርነትን እናድርግ፡፡ ከእኛ ይቅርታን ሽተው የመጡትን ይቅር እንበላቸው፡፡ በዛሬዋ ቀን የፍጥረት ጌታ የሆነው እርሱ ከባሕርይው ውጪ የሰውን ተፈጥሮ ገንዘቡ አድርጎ በሥጋ ተገልጦአልና፣ እኛም ወደ ክፉ ፈቃድ የሚወስደንን ዐመፃ ከእኛ ዘንድ አርቀን በአዲስና እርሱ በሰጠን መንፈሳዊ ተፈጥሮ እንኑር፡፡… እኛ በአምላክ ማኅተም እንድንታተም እርሱ አምላክነቱን ከእኛ በነሳው ሥጋ አተመው፡፡ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡

የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር ፍቅሩን እያሰብን በኃጢያታችን ምክንያት ከልባችን ያወጣነው ሁሉ ዛሬም በልባችን እንዲወለድ ያስፈልጋል፡፡ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት አለ?” ማቴ. 2÷1

 

እግዚአብሔር ለምን ሰው ሆነ?

 

ከንጹሕ ባሕርይ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በደስታ ይኖር የነበረ ሰው የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፉ ከንጽህና ወጥቶ ኃጢአትን ለበሰ:: ሕይወቱን አስወስዶ ሞትን ተቀበለ:: የእግዚአብሔር ልጅነቱን አስቀርቶ የዲያቢሎስ ምርኮ ሆነ:: ደስታውን አጥቶ ኃዘን አገኘው:: ተጸጽቶ የጥንት ሕይወቱንና ደስታውን ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፤ ንጹህ ባሕርይው ስላደፈበት የሞት ፍርድን ሊያስቀርለት አልቻለም::

ዳግማዊ አዳም የተባለ የፍቅር አምላክ፣ የሁሉ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሞት ፍርድን ሊያስቀር ኃጢአትን ደምስሶ ከሞት ፍርድና ከገሃነም ነጻ ሊያወጣ  ሰው ሆነ፤ ተወለደ:: “እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም።” 1ዮሐ 3:5

በዚህም መሰረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም ዘመነ ዮሐንስ መጋቢት ሀያ ዘጠኝ ቀን እሑድ ከቀኑ ሶስት ሰዓት ተጸነሰ:: በአምስት ሺህ አምስት መቶ አንድ ዓመተ ዓለም በዘመነ ማቴዎስ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ማክሰኞ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ተወለደ::

 

ገና-ጌና-ገኒን፤ልደት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በዓል ገና ወይም በዓለ ልደት በመባል ይታወቃል:: ገና የሚለው ቃል ገነወ አመለከ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ ነው:: የጌታችን ልደትም የአምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ የመሆን ምሥጢር የተገለጠበት ታላቅና ገናና ስለሆነ ገና ተብሏል:: አምላክ አለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል እንዲል ሃይማኖተ አበው::

የገና ጨዋታ

በሃገራችን በኢትዮጵያ የገና በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ደምቆ ይከበራል:: በተለይ በገጠሩ ያገራችን ክፍል ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘ አባቶችና እናቶች ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በገና ይደረድራሉ:: ወጣቶችም የገና ጨዋታ ይጫወታሉ:: “በገና” ስሙን ያገኘው በገና በዓል ወቅት የሚደረደር በመሆኑ ነው ሲሉ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ:: በሌላም ትውፊት በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶችና አዛውንቶች የሚጫወቱት የገና ጨዋታ ራሱን የቻለ ባህልና ትውፊት አለው:: የገና ጨዋታ ራሱ በተቆለመመ በትርና ሩር የተባለ ከዛፍ ሥር በተሠራ ክብ እንጨት(ኳስ) እያጎኑ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡

ሰብአ ሰገል በኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተልሔም ሲሔዱ “የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት አለ” በማለት ቢጠይቁ ይህንን አስደንጋጭ ጥያቄ የሰማው ንጉሥ ሔሮድስ “እኔ ንጉሥ ሆኜ ሳለሁ ሌላ ንጉሥ እንዴት ይወለዳል” በማለት የተወለደውን ንጉሥ ለመግደል አገልጋዮቹን ከሰብአ ሰገል ጋር ሄደው ቦታውን አይተው እንዲመለሱ ላካቸው፡፡ የሔሮድስ አገልጋዮች ከተቀላቀሉ በኋላ እየመራ ያመጣቸው ኮከብ ጌታ የተወለደበትን ቦታ መምራቱን አቆመ፡፡ ሰብአ ሰገል ተጨንቀው “የኮከቡ እርዳታ ለምን ተለየን” ብለው ሲመረምሩ ከነሱ ዓላማ ውጭ ሌላ ሀሳብና ተንኮል ይዘው የተገኙ ሰዎችን አገኙ፡፡ “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔርን እርዳታ አጣን”፡፡ ብለው ሦስቱም ነገሥታት(ሰብአ ሰገል) ከአንዱ ወደ አንዱ እየተቀባበሉ በብትር እየመቱ አስወገዷቸው፡፡

ኮከቡም እየመራ ጌታ በተወለደበት ቦታ ቤተልሔም አደረሳቸው ከእረኞችና ከመላእክት ጋራ አመሰገኑት፡፡ እረኞች ጌታ በተወለደ ጊዜ ጨለማ ተሸንፎ አካባቢያቸው በብርሃን ተመልቶ መንፈስ ቅዱስ በገለጸላቸው ምስጢር ከመላእክት ጋራ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ሥምረቱ ለሰብእ” እያሉ ሲያመስግኑና ሲደሰቱ አድረዋል፡፡ በአሉ እረኞች ክብር ያገኙበት ምስጢር የተገለጠላቸው ስለሆነ በስነ ቃል “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለም በጨዋታ እንደሚከበር እንደሆነ አበው ይናገራሉ፡፡

ይህ ትውፊት የገና ጨዋታ እየተባለ ወጣቶች አዛውንቶች በጨዋታ ያከብሩታል፡፡ ራሱ የተቆለመመውና ሩሯን የሚያጎነው በትር የጌታችን ምሳሌ ሲሆን ሩሩ ደግሞ የሳጥናኤል ምሳሌ ነው:: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድረጎ የሰውን ሥጋ በመልበስ ወደዚህ ምድር እንደመጣና በሩር የተመሰለውን ሰይጣንን እንደቀጠቀጠው የሚያሳይ ምሥጢር ያለው ጨዋታ ነው::

ቤተ መቅደስ ገባች

 

በቀናችው መንገድ  በሃይማኖት ጸንተው፣

በቅዱስ ጋብቻ ትእዛዙን አክብረው፣

ምግባር ከሃይማኖት አሰተባብረው  ይዘው፤

ጸሎት ያልተለየው ቅዱስ ሕይወታቸው፣

ኢያቄም ወሐና ልጅ ወልዶ ለመሳም ቢፈቅድም ልባቸው፣

ሳይወልዱ ሳይከብዱ ገፋ ዘመናቸው።

ጸሎታቸው ቢደርስ   ልጅን ቢሰጣቸው፣

ብጽዓት ነውና ከአምላክ ውላቸው

የአምላክ አያት ሆነው ድንግልን ሰጣቸው፡፡

ሐናና ኢያቄም  ከሁሉም ልቀዋል፣

ፈጣሪን የምትወልድ ድንግልን ወልደዋል።

ጸሎት ያልተለየው ቅዱስ ሕይወታቸው፣

የፈጣሪን እናት መውለድ አስቻላቸው።

የሐና የኢያቄም የከበረች ፍሬ፣

ምስጋና እየሰማች ውዳሴ ዝማሬ፣

በቤተ መቅደስ ውስጥ ልትኖር አገልግላ፣

ገባች ቤተ መቅደስ ሦስት ዓመት ስትሞላ።

ሐና ሰጥታት ስትሄድ አድርሳት ከመቅደስ፣

ድንግል ወደ እናቷ ስትሄድ ስትመለስ፣

ዝቅ አለ ፋኑኤል ከሰማይ ወረደ፣

በክንፎቹ ጋርዶ መግቧት ዐረገ።

የሦስት ዓመት ሕፃን ትንሽ ብላቴና፣

የበኩር ልጃቸው የኢያቄም የሐና፡፡

በክንፎቹ ጋርዶ መልአክ የመገባት፣

ቤተ መቅደስ ገባች የአማኑኤል እናት።

ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ ያለው፣

የኢሣይያስ ስብከት ፍጻሜው ደርሶ ነው።

አምላክን ለመውለድ ቀድማ የታሰበች፣

አሥራ-ሁለት ዓመት ቤተ መቅደስ ኖረች።

ኢያቄም ወሐና እናትና አባትሽ፣

ኅልም አይተው ነበረ ድንግል መጸነስሽ።

ተአምሩ ብዙ ነው እም አምላክ ልደትሽ፣

ቤተ መቅደስ ሆነ ድንግል ሆይ ዕድገትሽ።

ዝናብ የታየብሽ ትንሿ ደመና፣

አንቺ መሶበ ወርቅ ውስጥሽ ያለ መና።

«እንደ ልቤ» ብሎ አምላክ ስም የሰጠው፣

ከእረኝነት መርጦ ንጉሥ ያደረገው፣

በጸጋ ተመልተሽ ቢመለከት ከብረሽ፣

በግርማ በሞገስ ወርቅ ተጎናጽፈሽ፣

በሰማይ በክብር በቀኝ በኩል ቢያይሽ፡

ወትቀውም ንግሥት ብሎ ተቀኘልሽ።

የሁላችን_ተስፋ_የአዳም_የስብከት ቃል፣

የነቢያት ምሥጢር የሲና ሐመልማል፣

የሕዝቅኤል ራእይ የነቢያት ትንቢት፡

ቅኔው ለሰሎሞን መዝሙሩ ለዳዊት።

ተሰምቶ አይጠገብ ውዳሴሽ መብዛቱ፣

ለአባ ሕርያቆስ አንቺ ነሽ ድርሰቱ።

እናታችን ማርያም ጥዑመ ስም ያለሽ፣

ጥዑመ ስም ያለው ክርስቶስን ወልደሽ፣

ዓለም ይባረካል ይኸው እስከ ዛሬ፣

መድኃኒት ነውና ከአንቺ የወጣው ፍሬ።

የነደደው እሳት በሲና ሐመልማል፣

ምሳሌ ለድንግል ምሳሌ ነው ለቃል።

ያንን ነበር ያየው ሙሴ በድንቁ ቀን፣

መለኮት ማደሩን በድንግል ማኅፀን።

አባ ሕርያቆስ ውዳሴሽ በዝቶለት፣

የምስጋናሽ ነገር ምሥጢር ተገልጦለት፣

የክብርሽን ነገር በአድናቆት በማየት፣

ይመሰክር ጀመር በጣፈጠ አንደበት።

እግሩ ከምድር ሳይለቅ ሐሳብ አመጠቀው፣

በደመና ጭኖ የኋሊት ወሰደው።

ያሬድ በዝማሬው ንዑድ ክቡር ያለሽ፣

ድንግል እናታችን የገነት ቁልፍ ነሽ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

አብርሃም_ሰሎሞን።