ዘመነ ስብከት

በኩረ ፍሥሐ ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ዘመነ ስብከት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት፣ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ፣ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል ፤ ድኀረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት፣ መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን፣ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነ ፤ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትስብእቱ ፤ የሚባል ጌታ በተዋሕዶ ከበረ ብለን የቀናች የአባቶቻችን ሃይማኖታቸው ተዋሕዶን እንመሰክራለን፡፡

ስንዱዋ እመቤት ቤተክርስቲያናችን ወራትን እና ዘመናትን ከፍላ ነገረ ሃይማኖትን ታስተምራለች።አባቶቻችንም የወራቱንና የቀናቱን  የሰንበታቱንም ምስጢር በማገናዘብ የመጽሐፍ ቅዱስን ምንባባት ከቅዱስ ያሬድ መዝሙር ጋር በማዛመድ ግጻዌ የሚባልን መጽሐፍ ሰርተውልናል።

አባቶቻችን ሊቃውንት ከኅዳር ፮  እስከ  ስብከት  ያለውን ንዑስ ዘመን  ዘመነ አስተምህሮ ይሉታል፡፡ ስብከት የሚውለው ከታኅሣሥ ፯ እስከ  ፲፫  ባሉት ቀናት ውስጥ በሚውለው እሁድ በመሆኑ ፤ ዘመነ አስተምህሮ ዝቅ ብሎ  ከኅዳር ፮ እስከ ታኅሣሥ ፯  ወይም ከፍ ብሎ  ከኅዳር ፮  እስከ  ታኅሣሥ ፲፫ ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡

ዘመነ አስተምህሮ ከዘመነ ስብከት መቅደሙ እግዚአብሔር አዳምን ይቅር እንዳለው ለማጠየቅ ሲሆን፣ ከዘመነ አስተምህሮ ቀጥሎ ዘመነ ስብከት መባሉ ደግሞ አዳምን ይቅር ያለው ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔር አምላክ ሰው ሁኖ የሚወለድበት ዘመን እንደ ደረሰ ለማጠየቅ ነው፡፡

 

ስብከት ኢይወርዱ ታኅሣሥ ሰባት ሲሆን ኢየዐርጉ ደግሞ ታኅሣሥ ዐሥራ ሦስት ስለሆነ ከታኅሣሥ ሰባት እስከ ታኅሣሥ ዐሥራ ሦስት ባለው ይመላለሳል ፡፡

በዚህም ዕለተ ሰንበት  ሙሴ በኦሪት፥ ነቢያትም ስለ እርሱ ስለጻፉለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋዌ ትንቢቱን አውቆ ያናገረ ምሳሌውን ያስመሰለ ነቢያት አስቀድመው ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ ሰው ሆኖ  እንደሚያድነን ትንቢት መናገራቸውን ሱባኤ መቁጠራቸውን የሚነገርበት የሚሰበክበት በመሆኑ ስብከት ይባላል።

አባቶቻችን ስብከት የሚውልበትን ቀን የሚያሰሉት በወርኀ ታኅሣሥ መባቻ ፣ በነቢየ እግዚአብሔር በኤልያስ ክበረ በዓል ነው፡፡ የባህረ ሐሳቡን ትምህርት በመያዝ በቀላሉ ለማስታወስ ጥንተ ቀመርን ወይም የዕለታት ተውሳክን በመጠቀም ማስላት እንችላለን፡፡

ጥንተ ቀመርን በመጠቀም ስናሰላ

 

ስብከት ታኅሣሥ ፲፫ የሚሆነው ኤልያስ(ታኅሣሥ መባቻ)  በጥንተ ቀመር (በዕለተ ማክሰኞ)  የዋለ እንደሆነ ነው፡፡በዚህም መሰረት፦

  1. ታኅሣሥ 1 ማክሰኞ ከዋለ ፣ ስብከት ታኅሣሥ 13 ቀን ይውላል፡፡
    2. ታኅሣሥ 1 ረቡዕ ከዋለ ፣  ስብከት ታኅሣሥ 12 ቀን ይውላል፡፡
    3. ታኅሣሥ 1 ሐሙስ ከዋለ፣ ስብከት ታኅሣሥ 11 ቀን ይውላል፡፡
    4. ታኅሣሥ 1 አርብ ከዋለ ፣ስብከት ታኅሣሥ 10 ቀን ይውላል፡፡
    5. ታኅሣሥ 1 ቅዳሜ ከዋለ፣ ስብከት ታኅሣሥ 9 ቀን ይውላል፡፡
    6. ታኅሣሥ 1 እሑድ ከዋለ፣ ስብከት ታኅሣሥ 8 ቀን ይውላል፡፡

7.ታኅሣሥ 1 ሰኞ ከዋለ፣ ስብከት ታኅሣሥ 7 ቀን ይውላል፡፡

የዕለታት ተውሳክን በመጠቀም ስናሰላ

 

የዕለታት ተውሳክ በቅዳሜ ይጀምራል እርሱም ፰ ነው ፡፡ ቅዳሜ(8) ፣ እሁድ(7) ፣  ሰኞ(6) ፣ ማክሰኞ(5) ፣ ረቡዕ(4) ፣ ሃሙስ(3) ፣ ዓርብ(2)

በዚህም መሰረት፦

1.ታኅሣሥ 1 ቅዳሜ ከዋለ፣ ስብከት (1+8=9) ታኅሣሥ 9  ቀን ይውላል፡፡

2.ታኅሣሥ 1 እሑድ ከዋለ፣ ስብከት (1+7=8) ታኅሣሥ 8  ቀን ይውላል፡፡
3.ታኅሣሥ 1 ሰኞ ከዋለ፣ ስብከት (1+6=7) ታኅሣሥ 7 ቀን ይውላል፡፡
4.ታኅሣሥ 1 ማክሰኞ ከዋለ ፣ ስብከት (1+5=6 ይሆናል።ሰባት ስላልሞላ ሌላ ሳምንት ይፈልጋል ስለዚህ  6+7=13 ) ታኅሣሥ 13 ቀን ይውላል፡፡
5. ታኅሣሥ 1 ረቡዕ ከዋለ ፣  ስብከት (1+4+7=12) ታኅሣሥ 12 ቀን ይውላል፡፡
6. ታኅሣሥ 1 ሐሙስ ከዋለ፣ ስብከት(1+3+7=11)  ታኅሣሥ 11 ቀን ይውላል፡፡
7. ታኅሣሥ 1 አርብ ከዋለ ፣ስብከት (1+2+7) ታኅሣሥ 10 ቀን ይውላል፡፡

 

ምስባክ ዘስብከት መዝ ፻፵፫፥፯


‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም ፤

አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ፤

ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ  ነኪር ። ››

 

በስብከት (ከታኅሣሥ ፯ እስከ  ፲፫  ባሉት ቀናት ውስጥ በሚውለው እሁድ) ነቢያት የጌታን ሥጋዌ ማስተማራቸው ይነገርበታል ፡፡ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ልጅነቱን ካጣ ከገነት ከወጣ በኋላ ‹‹እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ያህል ቦታ በኃጢአቴ ምክንያት አጣው›› እያለ ሲያዝን ጌታ ኀዘኑን አይቶ ጸሎቱን ሰምቶ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅ ተወልጄ አድንኃለው›› ብሎ ተስፋ ሰጥቶታል፡፡  ከእሱ በኋላ የተነሱ ነቢያት በግዝረታቸው፣ በመስዋዕታቸው መዳን የማይቻላቸው ቢሆን ለአዳም በሰጠው ተስፋ ከሰማያት ወርዶ፣ ከድንግል ተወልዶ፣ በሕማሙ በሞቱ ያድናቸው ዘንድ ‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም  እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም››  እያሉ ተማጽነውታል፡፡

 

ፈኑ እዴከ እምአርያም

 

እድ መዝራዕት የሚባል ልጅህን በሥጋ ላክ አንድም ረድኤትህን ከአርያም ላክ፤ኢየሱስ ክርስቶስን እዱ መዝራዕቱ ለአብ ይለዋል።የሰው ኀይሉ በክንዱ እንዲታወቅ የአብም ኀይሉ በውልድ ይታወቃልና አንድም ክንድ ከአካል ሳይለይ የወደቀውን ዕቃ አንስቶ ይመለሳል እርሱም ከአብ አንድነት ሳይለይ አዳምን ያድናልና አድኗልና እንድም በክንድ የራቀውን ያቀርቡበታል የቀረበውን ያርቁበታል በርሱም ጻድቃንን ንዑ ኀቤየ ብሎ ያቀርብባታል ኃጥአንን ሑሩ እምኔየ ብሎ ያርቅበታልና ነው።

 

አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ

 

በሥልጣንህ ከብዙ መከራ ከብዙ ጦር አድነኝ ፤አንድም በልጅህ ከፍትወታት እኩያት ከኀጣውእ ከፍዳ ከመከራ ነፍስ ፈጽመህ አድነኝ።

ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ  ነኪር

 

ከዲያቢሎስ ወገኖች ሥልጣን አድነኝ አንድም ከባዕድ ልጆች እጅ አድነኝ።
ሀብተ ትንቢት የተሰጠው ቅዱስ ዳዊት የጌታን ልደት በተስፍ ተመልክቶ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎችን ትንቢቶች ተናግሯል።

 

በስብከት የሚነበቡ ምንባባት

 

በስብከት የሚነበቡ ምንባባት በዕለቱ መዝሙር ‹‹ወልዶ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ…››ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን በሚለው የቅዱስ ያሬድ ዜማ ተስማምተው የተዘጋጁ ናቸው።

 

በዚህ ዕለት የሚነበቡት ምንባባት፥ ነቢያት ሱባኤ እየገቡ ምሥጢር እየተገለፀላቸው ስለ ነገረ ሥጋዌው ትንቢትና በብዙ ምሳሌ መናገራቸውን እንዲሁም   ተስፋ ትንቢታቸው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መፈጸሙን የሚያስረዱ ናቸው።

 

    • ዕብ ፩፥፩-፲፬ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ አይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ….››

 

  • ፪ኛ ጴጥ ፫ ፥ ፩፡፲ ‹‹ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ ናት። በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ።በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤እነርሱም  የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው፧ አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።….››

 

  • የሐዋ ፫ ፥ ፲፯ ፡ ፳፮ ‹‹አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው።እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና።ሙሴም ለአባቶች። ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት።ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ።ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ።እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም። በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ።ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።››

 

 

 

ወንጌል ዘስብከት ዮሐ ፩፥፵፬፡፶፪

 

‹‹በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና ተከተለኝ አለው። ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው።

ናትናኤልም ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን አለው። ፊልጶስ መጥተህ እይ አለው።ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።

ናትናኤልም ከወዴት ታውቀኛለህ አለው። ኢየሱስም መልሶ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው።

ናትናኤልም መልሶ መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው።

ኢየሱስም መልሶ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።››

 

በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል  እንደምንረዳው ፊሊጶስ ናትናኤልን እንደጠራውና ፤ናትናኤልን ፊሊጶስ ሳይጠራው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ናትናኤልን  እንደሚያውቀው፤ ስለእርሱም ደግነት መናገሩን እናያለን።

አባቶቻችን ፊሊጶስ ሳይጠራህ በፊት ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ የሚለውን በአንድምታ ትርጓሜ አስቀምጠውልናል

  • በቅትለተ ሕጻናት ሄሮድስ ሕጻናቱን ሲያስፈጅ እናቱ በቀፎ አድርጋ ከበለስ ሥር ሠውራው ነበርና ያንጊዜ ያዳንኩህ እኔ ነኝ ሲል ነው
  • ሰው ገድሎ አስቀብሮ ነበርና አንድም  የጎልማሳ ሚስት ቀምቶ የማይገባ ሥራ ሲሰራ ነበርና አውቅብሀለሁ ሲለው ነው
  • ባለጸጋ ነው ከዚያ ሆኖ ወይፋፍን ሲያስፈትን ፈረስ በቅሎ ሲያሰግር ይውል ነበርና አውቅሀለሁ ሲለው ነው
  • ምሑረ ኦሪት ነው ከዚያ ሆኖ የተነገረው ትንቢት ደረሰ የተቆጠረው ሱባኤ ቀረ እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ይውል ነበርና አውቅልሃለሁ ሲለው ነው።
  • የበለስ ቅጠሉ ሰፊ እንደሆነ ኃጢአት ሰፍናብህ አየሁህ ሲለው ነው።

በዚህም የስብከትና የትምህርት ዕለት ነገረ ሥጋዌው እና የነቢያት ውረድ ተወለድ አድኅነን የሚል ጸሎትና ልመና በሚታሰብበት ሰንበት ፤ ሁላችንም እራሳችን በቃለ እግዚአብሔር መክረን የአምላካችን ውለታ ማሰብ ያስፈልገናል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር