ክብረ ክህነት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ክብረ ክህነት

ክፍል አንድ፡  አጀማመሩና ሥርዓቱ

ክህነት ተክህነ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ፣የተገኘ ቃል ሲሆን አገለገለ ማለት ነው።መሥዋዕት ፣ጸሎት ልመና ወደ እግዚአብሔር እያቀረቡ ሰውና እግዚአብሔርን ማስታረቅ፣ እግዚአብሔር አምላክ ይቅር እንዲል ዘወትር በመሥዋዕቱ ፊት እየቆሙ መጸለይ ምሕረትን ፣ይቅርታን ከእግዚአብሔር ማሰጠት፤ ህዝቡ ደግሞ ኃጢአት እንዳይሠሩ ፣ሕገ እግዚአብሔርን እንዳይተላለፉ መምከር፣ማስተማር፣መገሰጽ መቻል ሲሆን በአጠቃላይ ክህነት ማለት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የቆመ ምሰሶ፣ መሰላል ወይም ድልድይ ማለት ነው። ሰውና እግዚአብሔር ይገናኙበታልና።

የክህነት አገልግሎት የተጀመረው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ነው።ዓለም የሚለው ቃል በራሱ ብዙ ትርጉም ያለው ሲሆን በአንድ በኩል የሰው ልጅ እራሱ ዓለም ይባላል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ፤ “ኢኃደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናተ ወዲያቆናት…” እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከመፍጠሩ በፊትም ሆነ ከፈጠረ በሁዋላ ምድርን ያለካህናትና ዲያቆናት አልተዋትም ማለት ነው። በሥነ-ፍጥረት ቅደም ተከተል መሠረት የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊት ቅዱሳን መላእክት እንደተፈጠሩ እና የክህነት አገልግሎትን እንደጀመሩ እንረዳለን። በመጽሐፈ ቅዳሴም፤ “እምቅድመ ይፍጥር መላእክተ ለቅዳሴ ኢተጸርአ ስብሐተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” ሲል መላእክትን እንኳን ለምስጋና ከመፍጠሩ በፊት በአንድነት በሦስትነት መመስገኑ በባህርይው ያልተቋረጠ መሆኑን ነው የሚያስረዳን።

ወደ ሰው ልጅ የክህነት አገልግሎት ስንመጣ ደግሞ በሦስት አበይት ክፍላተ ዘመን መድበን ማየት እንችላለን። በዘመነ ሕገ ልቡና፣ በዘመነ ብሉይ ኪዳን እና በዘመነ ሐዲስ ኪዳን ብለን።

ክህነት በህገ ልቦና፤ የቤተሰብ ክህነት በመባል ይታወቅ ነበር። ምክንያቱም መሥዋዕቱ የሚሰዋው፣ ጸሎቱ የሚጸለየው፣ ልመናው፣ሥርየቱ ስለቤተሰብ ብቻ ስለነበረ ነው። ለዚህም መነሻው አባታችን አዳም ራሱ ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፍ ዕፀ በለስን በልቶ፣ኃጢአት ሠርቶ፣ ከገነት በወጣና ከፈጣሪው በተለየ ጊዜ ንሰሐ ገብቶ፣ መሥዋዕት ሠውቶ፣ ወደፈጣሪው ባመለከተ ጊዜ ንሰሐን የሚቀበል እግዚአብሔር ንስሐውን ተቀብሎ የተስፋውን ቃል ሰጠው። ይህም ቃል “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እተወለድ እምወለተ ወለትከ…” አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፤ ህፃን ሆኜ፣ በምድርህ ተመላልሼ፣ በመስቀል ላይ በዕለተ ዐርብ ተሰቅዬ በሞቴ አድንኃለሁ የሚለው ነው። ይህም ቃል በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ በመጀመርያው ክፍል የሚገኘው ሲሆን ቅዱስ ያሬድም በድጓው በዜማ እያዋዛ፣ እያቀነባበረ በተደጋጋሚ ሲያመሰጥረው እናገኛለን።

ኢዮብም ምናልባት ልጆቼ እግዚአብሔርን በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር። ኢዮብም ማልዶ ተነስቶ እንደቁጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ እንደሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር። ኢዮ 1፣ 5። ጻድቁ ኖኅም ከማየ አይህ በሁዋላ መሥዋዕት እንደሠዋ እና እግዚአብሔር የገባለትን ቃል ኪዳን መሐላውንም በቀስተ ደመና ምልክት እንዳጸና ይህችም ቀስተደመና የድንግል ማርያም ምሳሌ መሆኗን ኢትዮጰያዊው ሊቅ አባ ጽጌ ድንግል “ቀስተደመና ማርያም ትዕምርተ ኪዳኑ ለኖኀ ዘእግዚአብሔር ሤመኪ ለተዝካረ ምሕረተ ወፍትህ…” እግዚአብሔር ለዓለም ድኀነት ያቆማት የቀስተደመናዋ ምሳሌ ድንግል ማርያም አንቺ ነሽ፤ እግዚአብሔር ለምሕረትና ለፍርድ ሹሞሻልና ሲል ነው።

አበ ብዙኀን አብርሃም ከሚታወቅባቸው በጎ ሥራዎቹ አንዱ ሁል ጊዜ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በማቅረቡ ነው።በዚህም ከመሥዋዕት ሁሉ የሚበልጠውን አንድ ልጁን ይስሐቅን ሳይቀር በቆራጥነት ለመሥዋዕት እንዳቀረበ እናያለን። በዚህ ሥራውም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። በሕገ ልቦና ሁሉም አባቶች መሥዋዕት ለማቅረብ ባለድርሻ ቢሆኑም ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ምሳሌ ናቸው።እዚህ ላይ ለየት ያለው ሌላው ክህነት የመልከጼዴቅ ክህነት ነው። ይህ የአዲስ ኪዳን ምሳሌ ሲሆን እራሱ መልከጼዴቅም የክርስቶስ ምሳሌ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው የሕገ ልቦና ክኅነት የቤተሰብ ክኅነት የተባለበት ምክንያት መሥዋዕቱ ለራሱና ለቤተሰብ ብቻ እንጂ ሌላውን የሚያካትት መሥዋዕት፣ ጸሎት ልመና ባለመሆኑ ነው። ብዙኃኑን አለማካተቱ ብቻ ሳይሆን የሚያስገኘውም ሥርየት ጊዜያዊ ሥርየት ማለትም ከአባር፣ ከቸነፈርና ከመቅሠፍት የሚያድን ሥጋዊ ድኀነት ብቻ እንጂ ነፍሳዊ ድኀነትን የማያካትት በመሆኑ ነው።

ክህነት በብሉይ ኪዳን፤  ከአሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች በነገደ ሌዊ የተላለፈ ሲሆን የቤተሰብ መሆኑ ቀርቶ የነገድ ክህነት መሆኑን እናያለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን ይህ ሥርዓት የተጀመረው በእግዚአብሔር ወዳጅ በሙሴ አማካይነት ሲሆን ሙሴ ቀጥታ ከእግዚአብሔር በመነጋገር የመሠረተው ስለሆነ ሕጉ፣ሥርዓቱ ከእግዚአብሔር የተሰጠ እንጂ ሰው ሠራሽ ባለመሆኑ እስከ ሐዲስ ኪዳን ዘመን ድረስ አገልግሎአል። ካህናቱም ከመሥዋዕት፣ጸሎት፣ ተግሣጽና ምክር በተጨማሪ ትንቢት የመናገር ሀብት ያላቸውም ነበሩ። ከእነዚህም ነገሥታት፣ ነብያት፣ መሣፍንት ይገኙበታል። በዚህ ዘመን ውስጥ ግን ክህነቱ ተሰጥቶአቸው ድርሻቸውን በአግባቡ የተወጡ ብዙዎች ሲሆኑ ባለመወጣታቸው እና ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ክህነት ባለመጠበቃቸው የተቀጡም አሉ። ለምሳሌ የኤሊ ልጆች አፍኔ እና ፊንሐስ እራሳቸው እነደጠፉ ታቦተ ሕጉንም እንዳስማረኩ ህዝቡንም እንዳጠፉና እንዳዋረዱ እናያለን። ክህነት ሳይፈቀድላቸው በጉልበት፣ በትምክሕት ተነሳሥተው ለማገልገል ሞክረው የጠፉም አሉ። በሙሴና በአሮን ዘመን የነበሩ ዳታን አቤሮን ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

ክህነት በሐዲስ ኪዳን፤ ደግሞ የተመሠረተው በራሱ በባለቤቱ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “ለሊሁ ሠዋዒ ወለሊሁ ተሠዋዒ” ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ምልእክቱ እንዳስተማረን እራሱ መሥዋዕት እራሱ ካህን (የመሥዋዕቱ አቅራቢ) ሆኖ ነው ያዳነን። ዕብ ፲፣፲፪ ይህም ክህነት የእርሱ የባህርይው ሲሆን ለቅዱሳን ሐዋርያት ደግሞ ጸጋውን በመሥጠት ከእነርሱ ቀጥሎ በእነርሱ ለሚተካ አምኖ፣ ተጠምቆ፣ ተምሮ እንዲሁም ሕጉን፣ ትዕዛዙን፣ ሥርዓቱን ጠብቆ ለተገኘ ሁሉ ትምህርቱ፣ እምነቱና ትህትናው እየታየ ዘር፣ቀለም፣ቋንቋ፣ነገድ፣ ሥልጣን ፣ሀብት፣ ቦታ ሳይለይ ሁሉም መሾም እንደሚችሉ ሥልጣን ሰጠ። ይህ ሥልጣን እስከ ዓለም ፍጻሜ የማሠር፣የመፍታት፣ መንግሥተ ሰማያትን የመዝጋትና የመክፈት ሥልጣን፣ ይቅር ላላችሁዋቸው ይቅር እላቸዋለሁ፤ይቅር ላላላችሁአቸው ግን ይቅር አልላቸውም የተባለልን ቅዱስ ጴጥሮስን ትወደኛለህ ብሎ ሦስት ጊዜ በመጠየቅ በጎቼን ጠብቅ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ ግልገሎቼን ጠብቅ ያለበት የመጠበቅ የማሠርና የመፍታት፣ ይቅር የማለት ሥልጣን ነው። መናዘዝ ማለት በኃጢያቱ ተጸጽቶ ከእግዚአብሔር ይቅርታን ለማግኘት ወደ ካህን የቀረበን ተነሳሂ፤ ንሥሐን ሰጥቶ በንሥሐ ሥርየት ወደ አምላክ ማቅረብ ማለት ነው።

ይህ ክህነት ለህዝብ፣ ለአህዛብ ሁሉ፣ እንዲሁም ለአመነ፣ ለተጠመቀና ለተማረ ሥለተፈቀደ፡ ክህነተ ብዙኃን ይባላል። አሰጣጡ ግን ሕግና ሥርዓት አለው። ከቅዱሳን ሐዋርያት ተያይዞ የመጣ በመሆኑ የነሱ ተተኪዎች በሆኑት በብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ካልሆነ በቀር በሌላ አይሠጥም ወይንም አይሰየምም።

ይቆየን!

ርእሰ ደብር ብርሃኑ አካል