Posts

ዘኒቆዲሞስ (የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት)

ዘኒቆዲሞስ (የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ፡፡ ከመ ትኩን መምሕረ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ፡፡

ትርጉም፡ ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ወደ ኢየሱስ ሂዶ ኢየሱስን ታላቅ መምህር ሁነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እኛ እናምንብሃለን፤ አንተ የአንበሳ ደቦል ክርስቶስ እንደ አንበሳ ሽምቀህ ትነሣለህ በመነሣትህ አንሣኝ አለው፡፡

መዝሙሩንና ምንባባቱን በዜማ ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

መልዕክታት

የኒቆዲሞስ ምንባብ 1 ( ሮሜ. ፯ ቊ. ፩ – ፲፱)

ወንድሞች ሆይ፥ ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ ሕግ እንዲገዛው አታውቁምን? ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች። ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሳለ ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች፤ ባልዋ ቢሞት ግን ከሕጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አይደለችም። እንዲሁ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፤ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ፥ እናንተ ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ። በሥጋ ሳለን በሕግ የሚሆን የኃጢአት መሻት ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በብልቶቻችን ይሠራ ነበርና፤ አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፥ ከሕግ ተፈትተናል፥ ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም። እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ። አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና። ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና።እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠችውን ትእዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፤ ኃጢአት ምክንያት አግኝቶ በትእዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል። ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት። እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም፥ ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር። ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ። በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።

የኒቆዲሞስ ምንባብ ወንጌል ( ዮሐ. ፫ ቊ. ፩ – ፲፪)    

ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።

የኒቆዲሞስ ምንባብ 3 (ሐዋ. ፭ ቊ. ፴፬ – ፵፪)

ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥ እንዲህም አላቸው። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ። ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።ሰሙትም፥ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር፡፡

ምስባክ  ( መዝ. ፲፮ ቊ. ፫ – ፬)

ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረክ በዓመጸ በላዕሌየ ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመሕያው፡፡

ትርጉም፦ ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ፈተንኸኝ፥ ምንም አላገኘህብኝም። የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፤ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ።

የኒቆዲሞስ ምንባብ 2 (፩ኛ ዮሐንስ. ፬ ቊ. ፲፰ – ፳፩

ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ። መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው። ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው።ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?

ቅዳሴ: ዘእግዝእትነ (ጎሥዓ)

ዘገብርኄር (የዐቢይ ጾም ሰድስተኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምዕመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሰይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ፡፡ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምዕመን ዘበውኁድ ወምእመን ዘበውኁድ ምዕመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡

ትርጉም፡ ጌታው መልካም ሲሠራ አግኝቶ በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚሾመው ቸርና ታማኝ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር በታናሹ የታመንህ ደግና ታማኝ አገልጋይ ሆይ በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡

መዝሙሩንና ምንባባቱ በዜማ ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

መልዕክታት

 ምንባብ 1 ( ፪ኛ ጢሞ. ፪ ቊ. ፩ – ፲፮)
እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል።የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ። በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ። ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤ ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና። ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤ ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው::

ምንባብ 2 (፩ኛ ጴጥ. ፭ ቊ. ፩ – ፲፪)
እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁምል ያበረታችሁማል። ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።

ምንባብ 3 (ሐዋ. ፩ ቊ. ፮ – ፱)
እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። እርሱም። አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።

ምስባክ ( መዝ. ፴፱ ቊ. ፰ – ፱)
ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ::
ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራሁ፡፡

ወንጌል ( ማቴ. ፳፭ ቊ. ፲፬ – ፴፩)

ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል።

ቅዳሴ: ዘባስልዮስ

ዘደብረ ዘይት (የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ፡፡ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ፡፡ ወዘአዝለፈ ትእዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን :: ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር፡፡ ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ፡፡ ወበአዕላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእምኅበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚአ ለሰንበት፡፡

ትርጉም፡ ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ ፤ እስከ መጨረሻ የጸና እርሱ ይድናል፡፡ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማያትና የምድር ኃይላት ሁሉ ይናወጣሉ፡፡ ያን ጊዜ በምድር ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለቅሳሉ አላችው፡፡ ጌታችንም ራሱ እንደተናገረ በተእዛዝ ፣ በመላእክትም አለቃ ድምፅና በመለከት ድምጽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ ወደ ምድር ይመጣል፡፡ እርሱ የሕይወት መገኛ ነውና ያን ጊዜ በኃጢአት ከመሞት ይራራልን፡፡

መዝሙሩንና ምንባባቱ በዜማ ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

መልዕክታት

ምንባብ 1( ፩ኛ ተሰሎንቄ ፬ ቊ. ፲፫ – ፍም)
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።

ምንባብ 2( ፪ኛ ጴጥ. ፫ ቊ. ፯ – ፲፭)
አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ።

ምንባብ 3 ( ሐዋ. ፳፬ ቊ. ፩ – ፳፪)
ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዡ አመለከቱት። በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ ይከሰው ዘንድ ጀመረ እንዲህ እያለ። ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን። ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፥ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፥ ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ። አይሁድም ደግሞ። ይህ ነገር እንዲሁ ነው እያሉ ተስማሙ።ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል። ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደ ሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ።ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ። ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤ ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ። ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደ ሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ። ወይም በመካከላቸው ቆሜ። ዛሬ ስለ ሙታን መነሣት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር፥ በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ በእኔ አንድ ዓመፃ ያገኙ እንደ ሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ። ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና። የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ ብሎ ወደ ፊት አዘገያቸው።

ምስባክ ( መዝ. ፵፱ ቊ. ፪ – ፫)
እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ ወአምላክነሂ ኢያረምም፤ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ።
ትርጉም፦ እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል።

ወንጌል (ማቴ. ፳፬ ቊ. ፩ – ፴፮)
ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ። ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም። ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ።እንግዲህ። እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።

ቅዳሴ: ዘአትናቴዎስ

መፃጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ሠርዓ ወይቤልዎ አይሁድ በዓይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ ወይቤሎሙ ኢየሱስ አነኒ እገብር አንትሙኒ እመኑ ለግብርየ ወይቤሎሙ አነ ዉእቱ እግዚአ ለሰንበት እግዚአ ዉእቱ ለሰንበት ወልድ ዋህድ ወይቤሎሙ ብዉህ ሊተ እኅድግ ኃጢአተ በዲበ ምድር እስብክ ግዕዛነ ወእክሥት አዕይንተ ዕውራን አቡየ ፈነወኒ

ትርጉም: የአዳም ፈጣሪ ለእረፍት ሰንበትን ሠራ፡፡ አይሁድም በማን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ አሉት፤ እርሱም እኔ እሠራለሁ እናንተም ሥራዬን እመኑ አላቸው፡፡ የሰንበት ጌታ እኔ ነኝ፤ የሰንበት ጌታዋ የአብ አንድያ ልጁ ነው፡፡ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር እል፤ ነፃነትን እሰብክ፤ የዕውራንን ዓይን አበራ ዘንድ አባቴ ልኮኛል አላቸው፡፡

መዝሙሩንና ምንባባቱ በዜማ ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

መልዕክታት

ምንባብ 1 (ገላ ፭ ቊ. ፩ – ፍም)

በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ። ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።

ምንባብ 2 (ያዕ. ፭ ቊ. ፲፬ – ፍም)

ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት ፡፡ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።

ምንባብ 3 (ሐዋ . ፫ ቊ. ፩ – ፲፪)

ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ።እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ። ወደ እኛ ተመልከት አለው። እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። ጴጥሮስ ግን። ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና፥ ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፥ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ። ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፤ መልካምም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ ስለ ምጽዋት ተቀምጦ የነበረው እርሱ እንደ ሆነ አወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መደነቅና መገረም ሞላባቸው። እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ?

ምስባክ

መዝ. ፵፩ ቊ. ፫ – ፬
እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ ፡፡ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ:: አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፡፡
ትርጉም፦ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል።
እኔስ። አቤቱ ማረኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት አልሁ።

ወንጌል (ዮሐ. ም. ፭ ቊ. ፩ – ፳፭)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ። ልትድን ትወዳለህን? አለው። ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ። ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት። እርሱ ግን። ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት። ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና። እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።

ቅዳሴ: ዘእግዚእነ (ነአኩተከ)

 

 

ምስክርነት

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፰ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው ቃል «በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፤ በሰማርያ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቼ ትሆኑኛላችሁ» የሚል ነው፡፡

ይሁዳ ኢየሩሳሌምን የሚያጠቃልል ግዛት ነው፤በኢየሩሳሌም የጌታችን ተአምር የተፈጸመበት፤ ብዙ ሰው ስለ እርሱ የሰማበትም ከተማ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ይልቅ በይሁዳ ስለ ክርስቶስ የሚያውቁም የሚሰሙም ዝቅተኛ ናቸው፡፡ ሌላው ሰማርያ ነው፤ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር በሥርዓት አይተባበሩም፤ በመጽሐፍ ቁጥርም፤ በባህልም፤ በቤተ መቅደስም አይገናኙም፤ አንዱ አንዱን ይጸየፈዋል፡፡

እኛስ በሕይወታችን ውስጥ ለሃይማኖታችን እየመሰከርን ነው? ከሐዋርያት ሥራ እንደምናነበው ቅዱስ እስጢፋኖስ መከራ በተቀበለ ጊዜና በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላይ ሰይፍ በተመዘዘ ጊዜ ሁሉም ከኢየሩሳሌም እየወጡ ተጉዘዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን፤ ቤታቸውንና ሀገራቸውን ትተው ወደ አሕዛብ ሀገር ሄዱ፤ በሔዱበት ቦታ ግን ወንጌል ተሰበከች፤ እነርሱ በሥጋ ቢጎዱ ቤተ ክርስቲያን ግን ተጠቅማለች ፡፡ የእኛ ወገኖች ቻይና፤ ዓረብ፤ አውሮፓና አፍሪካ ገብተዋል፤ ኢትዮጵያዊ ዘር ምናልባት ያልገባበት አንታርቲካ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ እነርሱ በሄዱበት ሁሉ ወንጌል አስተማሩ የሚል መጽሐፍ ተጽፎልናል? ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ወንጌል ተሰበከ ሳይሆን የሚሰማው ተጣሉ፤ተበጣበጡ፤ይተማማሉ ይቀናናሉ የሚል ነው፤ ይህ ነው ወንጌል? ወንጌል የሰላም፤ የፍቅርና የደኅንነት ምንጭ ነው፤የብጥብጥ፤ የጦርነት ፤የጭቅጭቅ ግን አይደለም፡፡

ከሐዋርያት ዕጣ ፈንታ በገዛ እጁ በጠፋው በይሁዳ ምትክ ሰው ለመተካት ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ «ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል» ብለዋል፤ በሐዋርያት ሥራ ፩፥፳፪፡፡ ሁለቱን ሰዎች ዕጣ የምንጥለው ለምንድን ነው? ለሚለው የሰጡት መልስ «ከሁለቱ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን» የሚል ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ፤ አስተማረ፤ ተያዘ፤ ተገረፈ፤ ተሰቀለ፤ሞተ፤ተቀበረ፤ተነሣ የሚለው ቃል የትንሣኤው ምስክር ነው፡፡

እኛስ የማን ምስክር ነን? ብዙዎቻችን ጥሩ የፊልም ተዋናዮች ነን፤ ስለ እነርሱ ተናገሩ ብንባል የምንናገረውን ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ተርኩ ብንባል አንተርክም፡፡ ስለ አንድ ዘፋኝ የምንናገረውን ያህል ስለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፤ ስለ ቅዱስ ያሬድ ተናገሩ ብንባል አንናገርም፤ የፊልም ተዋናዮቹንና የዘፋኞቹን ፎቶ ደረታችን ላይ ለጥፈን እየተንጠባረርን የምንሄደውን ያህል የቅዱሳንን ሥዕል በቤታችን ለመስቀል እናፍራለን፡፡ ታዲያ የማን ምስክሮች ነን? ዛሬ ኢትዮጵያውያንን በየቦታው እያጨቃጨቀን ያለው ስለ ምግብ ነው? ይበላል ወይስ አይበላም፤ ያገድፋል ወይስ አያገድፍም፤ የማያገድፍ ነገር በዚህ ምድር ላይ መተው ብቻ ነው፡፡

የሁላችንም ምስክርነት የትንሣኤው መሆን አለበት፤ ለምን የትንሣኤው የሚለውን መረጡ? ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ መነሣቱንና በሞት ላይ፤ በዲያብሎስ ላይ ኀይል እንዳለው፤ የተረዳነው በትንሣኤው ስለሆነ ነው፡፡ የትንሣኤው ምስክር ነው ወይስ ነገ የምንቃጠለውን ቃጠሎ ዛሬ እየመሰከርን ነው?‹‹እነሆ ቀን እንደ እሳት እየነደደ ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፤ ሚል.፬፥፩፡፡

ምስክሮቼ ትሆናላችሁ የሚለው ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ለሐዋርያት ነው፤ በኋላ ግን ሃይማኖታቸውን የገለጡ፤ ያስፋፉ፤ የመሰከሩ፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአሕዛብ የሰበኩ ሁሉ ምስክሮች ተብለዋል፡፡ ጌታም በወንጌል፤ «በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ» ብሏል፤ ማቴ. ፲፥፴፪፡፡ ዛሬ ስለ ምስክሮች ስንሰማ በአእምሮአችን የሚመጡት እነዚህ ስለ እምነት ብለው በፈቃዳቸው መከራን መቀበል የቻሉ ምስክሮች ናቸው፡፡

ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና ታሪካዊ አመጣጣቸው

ዲያቆን ተመስገን ዘገየ

ከትንሣኤ ሌሊት ፩ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያለው ሳምንት የፉሲካ ምሥጢር የተገለጠበት፤ ከግብፅ ወደ ምድረርስት ከሲኦል ወደ ገነት መሻገርን የሚያመላክት ሳምንት ነው። ለፉሲካ የሚታረደውም በግ ፉሲካ ይባላል (ዘዳ. ፲፮÷፪:፭÷፮)፤ ፉሲካ ማለት ደግሞ ማለፍ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትም ሳምንት የፉሲካ ሳምንት ነበር፤ (ሉቃ. ፳፪፥፲፬-፲፮፤ ዮሐ. ፲፰፥፴፰-፵)።

እርሱም ንጹሕ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን ፉሲካችን ክርስቶስ ተባለ፤ ብሉይ ደግሞ የሐዲስ አምሳል ነው። ይኸውም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ባሕረ ኤርትራን ካሻገራቸው በኋላ ወደ ምድረ ርስት፤ ነፍሳት ደግሞ በክርስቶስ መሪነት ከሲኦል ወደ ገነት መግባታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ዕለቱም ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፤ በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌ፤ግብፅ የሲኦል፤ የገሃነመ እሳት፤ የፈርዖን የዲያብሎስ፤ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ፤ እስራኤል የምእመናንና ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል ምሳሌ ነው፡፡

ሰኞ– ማዕዶት (ፀአተ ሲኦል)

ማዕዶት የቃሉ ትርጓሜ መሻገር ሲሆን፤ በዚህ ቀን ቤተ ክርስቲያን ነፍሳት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሐሳር ወደ ክብር፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት መሻገራቸውንና ፉሲካችን ክርስቶስ መሆኑን ታስባለች።

ማክሰኞ– ቶማስ

ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን፤ በቀኖት የተቸነከረው እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስም «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን» ብሎታል። ቶማስም «ጌታዬ አምላኬም»፤ ብሎ በመለሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስም «ስለ አየኸኝ አመንህን? ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓንስ ናቸው» አለው (ዮሐ ፳፥፳፯-፳፱)፤ ቶማስ የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን ስላመነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን ቶማስ ብላ ታስበዋለች።

ዲዲሞስ የተባለ ከአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙር አንዱ ቶማስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝግ ቤት ገብቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ባላቸው ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ አልነበረም»። ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ (ማቴ. ፲፥፪-፫) ቶማስ በአራማይክ ዲዲሞስ በግሪክ መንታ ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፳፥፳፬)፡፡ ቶማስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በፋርስና በሕንድ ወንጌልን እንዳስተማረ ይነገራል። ለቶማስ ጎኑን እንዲዳስስ የፈቀደው ለሌሎችም ቅዱሳን ሐዋርያት የተቸነከረውን እጅና እግሩን ያሳየው ካህናት ሥጋውና ደሙን እንዲፈትቱ ነው፤ ዮሐንስም በእጃችን ዳሰስነው ብሏል፤ (ሉቃ. ፳፬፥፴፱)፡፡

ለማርያም መግደላዊት ግን የተነሣ ዕለት አትንኪኝ ማለቱ ለሴቶች ሥጋውን ደሙን መፈተት አልተፈቀደም ሲል ነው ብለው ሊቃውንት ያትታሉ፤ «አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጅና፡- ወደ አባቴ÷ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ÷ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው» አላት፤ (ዮሐ. ፳፥፲፯)። ገቦ መለኮቱን የዳሰሰች እጁ በሕይወት ትኖራለች፤ በሕንድ ሀገር ከታቦት ጋር በመንበር ላይ ትኖራለች። በየዓመቱ በእመቤታችን በዓል በአስተርእዮ ሊያጥኑ ሲገቡ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች፤ ዓመት አገልግሎ ያርፋል።

ረቡዕ –አልዓዛር

አልዓዛር ክርስቶስ ያስነሣው የማርያምና የማርታ ወንድም ነው፤ የስሙም ትርጓሜ እግዚአብሔር ረድቷል ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፲፩፥፯-፵፰)፤ አልዓዛር የሞተው መጋቢት ፲፯ ነበር፡፡ እህቶቹም ክርስቶስ እንዲመጣ መልእክት ልከውበት ነበር፤ ክርስቶስ ግን በ፬ኛው ቀን ማለትም መጋቢት ፳ መጥቶ ከሞት አስነሥቶታል፤(ዮሐ.፲፩፥፵፬)፡፡ ፋሲካውንም በወዳጁ በአልዓዛር ቤት ያከብር ዘንድ ከቀደ መዛሙርቱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አስቀድሞ ላከ፤ ከዚያም በአልዓዛር ቤት ሆኖ የሐዲስ ኪዳንን ሥርዓት ምሥጢረ ቁርባንን ሰርቶ ለደቀ መዛሙርቱ አሳያቸው፤ አልዓዛር ከተነሣ በኋላ በሐዋርያት ኤጲስ ቆጶስነት ተሸሞ ፵ ዓመት አገልግሎ ግንቦት ፳፯ ቀን ዐርፏል (ስንክሳር ግንቦት ፳፯)፡፡

አዳም ሐሙስ

አዳም የመጀመሪያ ሰውና የሰው ሁሉ አባት ነው፤ በ፮ኛው ቀን የተፈጠረ የሰው ሁሉ ምንጭ ስለሆነ የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ፤ (ዘፍ. ፫÷፲፭) አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብበታል፡፡ ክርስቶስ በተነሳበት በአምስተኛው ቀን ሐሙስ አዳም ይባላል፤ ጌታችን አዳምን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ቃል ገብቶለት እንደነበር በቀሌምንጦስ ተጽፏል፡፡

አዳምና ሔዋን በገነት ፯ ዓመት ከቆዩ በኋላ ትእዛዙን በመተላለፋቸው ከኤደን ገነት አስወጣቸው (ኩፋ.፬፥፲፮፤ዘፍ.፫፥፳፫) «ብዙ ተባዙ» ያለው ቃል እንዳይቀር በምድር ላይ ወርደው ልጆችን ወለዱ ይላል፡፡ የተወለዱትም ልጆችም በቁጥር ፷ እንደሆኑ (፩መቃ. ፳፰፥፮) የተወለዱት ልጆች ደጎችና ክፉዎች እንደ ነበሩ በአቤልና በቃየል ታውቋል፤ (ዘፍ. ፬፥፰)፤ አዳም በዚህ ዓለም ፱፻፴ ዓመት ኑሮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፵፻፭፻፸ ሚያዚያ ፮ ዐርፏል፡፡

ዐርብ– ቤተ ክርስቲያን

ዐርብ የእግዚአብሔር ቅድስት ማደሪያ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ተሰይማለች፤ ይህም ሁሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ ነው፤ ዕለተ ዐርብ፤ የሥራ መከተቻ፤ ምዕራብና መግቢያ በሚሉት ስያሜዎችም ትጠራለች፡፡

በዕለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ያደረገውን ተአምር በመስቀሉ ድኅነትን እንዳሳየ፤ በቀራንዮ የሕንጻዋ መሠረት እንደተተከለላትና ሥጋ መለኮት እንደተቆረሰላት፤ ልጆቿን ከማሕፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ እንደፈሰሰላት ተገልጾባታል፤(ኤፍ.፪፥፲፱፤ራዕ.፩፥፮-፰)፡፡

ቅዳሜ– ቅዱሳት አንስት

ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፤ ይህም ስያሜ በስቅለት ዕለት በልቅሶና በዋይታ የሸኙትን፤(ሉቃ. ፳፫፥፳፯) በዕለተ ትንሣኤ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፤«ከሳንምንቱ በመጀመሪያዩቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ (ሉቃ. ፳፬ ፥ ፩ )፡፡

እሑድ– ዳግም ትንሣኤ

«ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና÷«ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው፤ ማቴ.፳፥፲፱፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ተሰውሮ ከሰነበተ በኋላ በዕለተ እሑድ በዝግ ቤት እንዳሉ ዳግም ተገለጸላቸው፤ስለዚህም ዳግም ትንሣኤ ተባለ፡፡

(ምንጭ:-መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ፤ ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ፤ ምዕ. ፳፥፳፬)

የሚያዝያ 18 ን ስንክሳር ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

የሚያዝያ 17 ን ስንክሳር ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

የሚያዝያ 16 ን ስንክሳር ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

የሚያዝያ 13 ን ስንክሳር ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ