ምስክርነት

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፰ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው ቃል «በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፤ በሰማርያ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቼ ትሆኑኛላችሁ» የሚል ነው፡፡

ይሁዳ ኢየሩሳሌምን የሚያጠቃልል ግዛት ነው፤በኢየሩሳሌም የጌታችን ተአምር የተፈጸመበት፤ ብዙ ሰው ስለ እርሱ የሰማበትም ከተማ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ይልቅ በይሁዳ ስለ ክርስቶስ የሚያውቁም የሚሰሙም ዝቅተኛ ናቸው፡፡ ሌላው ሰማርያ ነው፤ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር በሥርዓት አይተባበሩም፤ በመጽሐፍ ቁጥርም፤ በባህልም፤ በቤተ መቅደስም አይገናኙም፤ አንዱ አንዱን ይጸየፈዋል፡፡

እኛስ በሕይወታችን ውስጥ ለሃይማኖታችን እየመሰከርን ነው? ከሐዋርያት ሥራ እንደምናነበው ቅዱስ እስጢፋኖስ መከራ በተቀበለ ጊዜና በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላይ ሰይፍ በተመዘዘ ጊዜ ሁሉም ከኢየሩሳሌም እየወጡ ተጉዘዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን፤ ቤታቸውንና ሀገራቸውን ትተው ወደ አሕዛብ ሀገር ሄዱ፤ በሔዱበት ቦታ ግን ወንጌል ተሰበከች፤ እነርሱ በሥጋ ቢጎዱ ቤተ ክርስቲያን ግን ተጠቅማለች ፡፡ የእኛ ወገኖች ቻይና፤ ዓረብ፤ አውሮፓና አፍሪካ ገብተዋል፤ ኢትዮጵያዊ ዘር ምናልባት ያልገባበት አንታርቲካ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ እነርሱ በሄዱበት ሁሉ ወንጌል አስተማሩ የሚል መጽሐፍ ተጽፎልናል? ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ወንጌል ተሰበከ ሳይሆን የሚሰማው ተጣሉ፤ተበጣበጡ፤ይተማማሉ ይቀናናሉ የሚል ነው፤ ይህ ነው ወንጌል? ወንጌል የሰላም፤ የፍቅርና የደኅንነት ምንጭ ነው፤የብጥብጥ፤ የጦርነት ፤የጭቅጭቅ ግን አይደለም፡፡

ከሐዋርያት ዕጣ ፈንታ በገዛ እጁ በጠፋው በይሁዳ ምትክ ሰው ለመተካት ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ «ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል» ብለዋል፤ በሐዋርያት ሥራ ፩፥፳፪፡፡ ሁለቱን ሰዎች ዕጣ የምንጥለው ለምንድን ነው? ለሚለው የሰጡት መልስ «ከሁለቱ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን» የሚል ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ፤ አስተማረ፤ ተያዘ፤ ተገረፈ፤ ተሰቀለ፤ሞተ፤ተቀበረ፤ተነሣ የሚለው ቃል የትንሣኤው ምስክር ነው፡፡

እኛስ የማን ምስክር ነን? ብዙዎቻችን ጥሩ የፊልም ተዋናዮች ነን፤ ስለ እነርሱ ተናገሩ ብንባል የምንናገረውን ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ተርኩ ብንባል አንተርክም፡፡ ስለ አንድ ዘፋኝ የምንናገረውን ያህል ስለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፤ ስለ ቅዱስ ያሬድ ተናገሩ ብንባል አንናገርም፤ የፊልም ተዋናዮቹንና የዘፋኞቹን ፎቶ ደረታችን ላይ ለጥፈን እየተንጠባረርን የምንሄደውን ያህል የቅዱሳንን ሥዕል በቤታችን ለመስቀል እናፍራለን፡፡ ታዲያ የማን ምስክሮች ነን? ዛሬ ኢትዮጵያውያንን በየቦታው እያጨቃጨቀን ያለው ስለ ምግብ ነው? ይበላል ወይስ አይበላም፤ ያገድፋል ወይስ አያገድፍም፤ የማያገድፍ ነገር በዚህ ምድር ላይ መተው ብቻ ነው፡፡

የሁላችንም ምስክርነት የትንሣኤው መሆን አለበት፤ ለምን የትንሣኤው የሚለውን መረጡ? ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ መነሣቱንና በሞት ላይ፤ በዲያብሎስ ላይ ኀይል እንዳለው፤ የተረዳነው በትንሣኤው ስለሆነ ነው፡፡ የትንሣኤው ምስክር ነው ወይስ ነገ የምንቃጠለውን ቃጠሎ ዛሬ እየመሰከርን ነው?‹‹እነሆ ቀን እንደ እሳት እየነደደ ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፤ ሚል.፬፥፩፡፡

ምስክሮቼ ትሆናላችሁ የሚለው ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ለሐዋርያት ነው፤ በኋላ ግን ሃይማኖታቸውን የገለጡ፤ ያስፋፉ፤ የመሰከሩ፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአሕዛብ የሰበኩ ሁሉ ምስክሮች ተብለዋል፡፡ ጌታም በወንጌል፤ «በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ» ብሏል፤ ማቴ. ፲፥፴፪፡፡ ዛሬ ስለ ምስክሮች ስንሰማ በአእምሮአችን የሚመጡት እነዚህ ስለ እምነት ብለው በፈቃዳቸው መከራን መቀበል የቻሉ ምስክሮች ናቸው፡፡