መስቀል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

  ከጌታችንና ከአምላካችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በፊት መስቀል የመቅጫ መሣሪያ ነበር። ሰውን በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረውም በፋርስ ነው። ፋርስ የዛሬዋ ኢራን ናት። የፋርስ ሰዎች “ኦርሙዝድ” የተባለ “የመሬት አምላክ” ያመልኩ ነበር። ከዚህም የተነሣ “ወንጀለኛው ቅጣቱን በመሬት ላይ የተቀበለ እንደሆነ አምላካችን ይረክሳል፤” ብለው ስለሚያምኑ ወንጀለኛውን ከመሬት ከፍ አድርገው በመስቀል ላይ ይቀጡት ነበር። ይህም ቅጣት ቀስ በቀስ በሮማ ግዛት ሁሉ የተለመደ ሕግ ሆነ። ከዚህም ሌላ በኦሪቱ ሥርዓት ቅጣታቸውን በመስቀል ላይ የሚቀበሉ ሰዎች ርጉማንና ውጉዛን ነበሩ። ይህንንም እግዚአብሔር ለሙሴ “ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥ በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤” ሲል ነግሮታል። ዘዳ.21፥22-23። እዚህ ላይ “በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሚሞት የተረገመ ከሆነ፥ ለምን ጌታችን በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ?” እንል ይሆናል። ይህንንም እንደሚከተለው እናያለን።

“ለምን በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ?”

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶልናል፥ ክቡር ደሙን አፍስሶልናል፥ ክብርት ነፍሱንም በፈቃዱ አሳልፎ ሰጥቶልናል። ይህንንም ያደረገው በቤዛነቱ እኛን ከእርግማን ሊዋጀን ነው። ምክንያቱም የሰው ልጆች በጠቅላላ በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ ተይዘን ነበርና። በመሆኑም በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም፥ በሞተ ሥጋ ላይም ሞተ ነፍስ ተፈርዶብን ከእርግማን በታች ወድቀን ነበር። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን “እንደ ወጡ ሳይመለሱ፥ እንደወደቁ ሳይነሱ ይቅሩ፤” ሳይል እኛን ለመፈለግ ከሰማየ ሰማያት ወረደ። ማቴ.18፥12-14። በመንፈስ ቅዱስ ግብር በማኅፀነ ድንግል ማርያም ተፀነሰ። ሉቃ.1፥35። ከእመቤታችንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። ሉቃ.2፥7። በተዋህዶ ሰው አምላክ፥ አምላክ ሰው ሆነ። ማቴ.16፥13፣ 1ኛ ዮሐ.1፥1-2፤ 5፥20። ቀስ በቀስም አደገ። ሉቃ.2፥40። ሠላሳ ዓመት በሞላውም ጊዜ በፈለገ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾመ። ማቴ.3፥13-17፣ ሉቃ.3፥21-23፣ ማቴ.4፥2። ከዚያም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ሰባ ሁለቱን አርድዕትና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት መረጠ። የሐዋ.1፥15። አዲስ ሕግ ወንጌልንም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር አስተማረ። በመጨረሻም ሰለእኛ እርግማን /ኃጢአት/ ተላልፎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ። ማር.15፥23-37። የሞተውም በፈቃዱ ነው። ዮሐ.10፥11፤ 15፥13። በዚህም የዕለት ፅንስ ሆኖ በእመቤታችን ማኅፀን ጀምሮት የነበረውን የማዳን ሥራ በመስቀል ላይ ፈጸመው። ዮሐ.19፥30።

እንግዲህ ጌታችን ወደዚህ ዓለም መጥቶ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ የሞተው ከላይ እንደተጠቀሰው ስለ እኛ እርግማን ተላልፎ ነው። እርሱ በመስቀል ላይ እርግማናችንን /ኃጢአታችንን/ ሰለተሸከመልንም እኛ ከእርግማን /ከመርገመ ሥጋ፥ ከመርገመ ነፍስ/ ነፃ ሆነናል። ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፥ ሕመማችንንም ተሸክሟል፤ … እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፥ ስለበደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣፅ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።” ሲል አስቀድሞ የተናገረው ለዚህ ነው። ኢሳ.53፥4-5። ቅዱስ ጳውሎስም ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “በእንጨት የሚሰቀል ሁል የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና፥ ክርስቶስ ስለ እርግማን ሆኖ /ስለ እኛ ኃጢአት ተላልፎ በመስቀል/ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤” ብሏል። ገላ.3፥13። በቆሮንቶስ መልእክቱም “የእግዚአብሔር ማደሪያ ለመሆን እኛን ጻድቃን ያሰኘን ዘንድ ስለ እኛ ኃጢአት ተላልፎ ራሱን ኃጥእ አሰኝቷልና፤” ብሏል። 2ኛ ቆሮ.5፥21። ከዚህም ሌላ ለፊሊጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ይኸውም ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ፤” ብሏል። ፊል.2፥7-8። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በበኩሉ “እርሱ ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፥ ኃጢአታችንን /እርግማናችንን/ በእንጨት /በመስቀል/ ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ፤” ብሏል። 1ኛ ጴጥ.2፥22-24። በመሆኑም በመስቀል ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ብዙ ነገር አግኝተናል።

1ኛ. ሕይወትን አግኝተናል፤

በኃጢአት ምክንያት ሞት ገዝቶን ሞት ነግሦብን ነበር። ኃጢአት በዘር እየተላለፈም ሁላችንም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እንሞት ነበር። በመሆኑም ሞት ከአዳም እስከ ሙሴ /እስከ ክርስቶስ/ ድረስ ነገሠ። ሮሜ.5፥12-14። ከክርስቶስ በኋላ ግን በክርስቶስ ቤዛነት ሞት ስለተሻረ አጥተነው የነበረውን ሕይወት አግኝተናል። ለዚህም ነው “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፤” የተባለው። 1ኛ ቆሮ.15፥22። በተጨማሪም “እኛ ሁላችን ደግሞ፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበር እንደሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር /በክርስቶስ ቤዛነት/ ሕይወትን ሰጠን።” ተብሏል። ኤፌ.2፥3-5። ምክንያቱም ጌታችን በሞቱ ሞትን ሽሯልና። 2ኛ. ጢሞ.1፥10።

2ኛ. የሕይወትን ምግብ አግኝተናል፤

ኃጢአት ወደ ዓለም ገብቶ ሞትን ያመጣብን በመብል ምክንያት ነው። ዘፍ.3፥1-24። ምክንያቱም አዳምና ሔዋን የዕፀ በለስን ፍሬ በልተው ጐትተው ያመጡት ሞትን ነውና። ኢዮርብአምን እንዲገሥጽ ተልኮ የነበረውም የይሁዳ ሰው አትብላ የተባለውን በመብላቱ ያተረፈው ሞትን ነው። 1ኛ ነገ.13፥20-25። እስራኤል ዘሥጋም በምድረ በዳ የተመገቡት መና ከሞት አላዳናቸውም። ዮሐ.6፥49። ስለዚህ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ሥጋውን የሕይወት እንጀራ አድርጎ በመስቀል ላይ ሰጠን። ይህንንም “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ /የወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን/ ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤” ሲል አረጋግጦልናል። ዮሐ.6፥53-54። በመሆኑም ዕለት ዕለት በቤተክርስቲያን የሚሠዋውና በሃይማኖት የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን አማናዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና አማናዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። ምክንያቱም ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኰት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኰት ይሆናልና። ማቴ.26፥27-29። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና፤” ያለው። 1ኛ ቆሮ.11፥27-30።

3ኛ. ሰላምን አግኝተናል፤

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም፤” ብሎ እንደተናገረ ፍጹም የሆነውን ሰላም የሰጠን በመስቀል ላይ ነው። ይህንንም፡- ሞትን በኃይሉ ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል። ዮሐ.14፥27፤ 20፥19፣26። ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና፤” በማለት የቆላስይስን ሰዎች አስተምሯል። ቆላ.1፥19-20። የኤፌሶንን ሰዎችም “አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና /ሰላማችን የተገኘው በእርሱ ቤዛነት ነውና/፤” ብሏቸዋል። ኤፌ.2፥13።

4ኛ. አዲስ ሰው ሆነናል፤

በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ አርጅቶ የነበረው ሰውነታችን አዲስ የሆነው በመስቀል ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን /ሰውነታችን/ ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን።” ያለው ሮሜ.6፥6። ዳግመኛም በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ “ስለዚህ ማንም ቢሆን በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል፤” ብሏል። 2ኛ ቆሮ.5፥17። ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው፡- ጌታችን እኛን በቤዛነቱ አዲስ አድርጎናል፥ አዲስ ሕግ ወንጌልንም ሰጥቶናል፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር መንግሥተ ሰማያትንም አዘጋጅቶልናል። ማር.1፥15፣ 2ኛ ጴጥ.3፥13፣ ራእ.21፥1።

5ኛ. ታርቀናል፤

በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተን እንኖር ነበር። ይሁን እንጂ እኛ በበደልን እርሱ ክሶ በቤዛነቱ መልሶ ታርቆናል። ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን፤” ሲል ገልጦታል። ሮሜ.5፥10-11። በተጨማሪም “በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና፤” ብሏል። ቆላ.1፥20። በኤፌሶን መልእክቱም “ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛት ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድ አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር /ከራሱ/ ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፤” ብሏል። ኤፌ.2፥14-16፣ 2ኛ ቆሮ. 5፥17። በመሆኑም ይህ ሁሉ ነገር የተገኘበት መስቀል፡-

ኃይላችን ነው፤

“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፤” 1ኛ ቆሮ.1፥18 ተብሎ እንደተነገረ፥ የእግዚአብሔር ኃይሉ የተገለጠበት ኃይለ እግዚአብሔር ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የፈጸመው በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ነው። በመሆኑም የጌታችን ቅዱስ ሥጋው የተፈተተበትና ክቡር ደሙም የፈሰሰበት መስቀል ስለ ክርስቶስ የከበረ ነው። ለምሳሌ የሆሳዕና አህያ በተጓዘችበት ጐዳና ሁሉ የተነጠፈላትና የተጐዘጐዘላት ስለ ክርስቶስ የከበረች በመሆኗ ነው። ማቴ.21፥8። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የከበረውና የማዳን ኃይሉም የተገለጠበት መስቀል፥ ወልድ ዋህድ ብለን በኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ለምናምን ሁሉ ዲያብሎስን የምንቀጠቅጥበት ኃይላችን ነው። ምክንያቱም ጌታችን አስቀድሞ “እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤” ተብሎ እንደተነገረ ዲያብሎስን የቀጠቀጠው በመስቀሉ ነውና። ዘፍ.3፥15። ይህንን በተመለከተ በብሉይ ኪዳን ዘመን የተፈጸመ ምሳሌ አለ። የነቢያት አለቃ ሙሴ እጆቹን በመስቀል አምሳል ግራና ቀኝ ዘርግቶ በሚጸልይበት ጊዜ እስራኤል ኃይል አግኝተው ጠላቶቻቸውን ድል አድርገዋል። እኛም እስራኤል ዘነፍስ የምንባል ምዕመናንም ጠላቶቻችንን አጋንንትን በኃይለ መስቀሉ ድል እናደርጋቸዋለን። የአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል አባት ቅዱስ ያዕቆብም እጆቹን ባመሳቀለ ጊዜ ኃይል አግኝቶ በዮሴፍ ልጆች ላይ በረከትን አሳድሯል። ዘፍ.48፥13-20። እኛም በመስቀሉ ኃይል በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን እናገኛለን።

ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ግን ፊት በቀራንዮ ድል የሆነበትን፥ ኋላም እንደ ቀራንዮ ዕለት ዕለት የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ በሚፈተትባት በቤተክርስቲያን ድል የሚሆንበትን መስቀል ከእጃችን ለማስጣል ያልሞከረው ሙከራ የለም። ለልማዱም “እንጨት አይደል? ለምን ትሳለሙታላችሁ? ለምንስ ትሰግዱለታላችሁ?” እያሰኘ ነው። ይሁን እንጂ በቤተክርስቲያን በክርስቶስ ኃይል ይታመናል እንጂ “ይህ እንጨት ነው፥ ይህም ጨርቅ ነው፥ ይህ ደግሞ ውሃ ነው፤” ተብሎ አይጠረጠርም። ለምሳሌ፡-
•    በትረ ሙሴ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ብዙ ተዓምራት አድርጋለች፤ ከዘፀ.4-14
•    የኤልያስ መጐናጸፍያ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ዮርዳኖስን ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለሁለት ከፍላለች፤ 2ኛ ነገ.2፥7-14
•    ፈለገ ዮርዳኖስ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ንዕማንን ከለምጹ ፈውሳዋለች፤ 2ኛ ነገ.5፥1-14
•    በዘይት /በቀንዲል/ ላይ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦ በሽተኞች ተፈውሰዋል፤ ማር.6፥13፣ ያዕ.5፥14
•    የቤተሳይዳ መጠመቂያ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ዓይነ ስውሩ ብርሃን አግኝቶባታል፤ ዮሐ.9፥1-12
•    ቅዱስ ጳውሎስ የልብሱ ቁራጭ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦበት ብዙ በሽተኞች ፈውስ አግኝተውባታል፤ ከአጋንንት ቁራኝነትም ተላቀውባታል፤ የሐዋ.19፥11-12
•    ቅዱስ ጴጥሮስ ጥላው ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ከመንገድ ዳር የወደቁ በሽተኞች ሁሉ ተፈውሰውባታል። የሐዋ.5፥15። ስለሆነም ስለመስቀሉ ያልሆነ ነገር እየተናገርን ከመስቀሉ ባለቤት ከክርስቶስ እንዳንጣላ መጠንቀቅ አለብን። ምክንያቱም መስቀልን መጥላት የክፉ ትንቢት መፈጸሚያ መሆን ነውና። ይህንንም በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ አላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው /ገሃነመ እሳት ነው/፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው /አይጾሙም/፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው፤” ሲል ተናግሯል። ፊል.3፥18-19።

እንግዲህ ነቢዩ ዳዊት “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ፤” ብሎ አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረ፥ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዲያብሎስ ቀስት /ጦር/ እናመልጥና እንድን ዘንድ በደሙ ቀድሶና አክብሮ የሰጠንን ምልክት መስቀልን አጥብቀን መያዝ አለብን። መዝ.59፥4-5። እንደ ቅዱስ ጳውሎስም “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት /ዓለም በእኔ ዘንድ ሙት ከሆነበት/ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት /እኔም በዓለም ዘንድ ሙት ከሆንኩበት/ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” እያልን በመስቀሉ መመካት አለብን። ገላ.6፥14። መስቀልን በምልክትነቱ ብቻ የሚቀበሉት ሰዎች አሉ፤ ለእኛ ግን መስቀል ኃይላችን፥ መድኃኒታችን፥ የሚያድነን፥ ቤዛችንና የነፍሳችንም መዳኛ ነው። ከዚህ ቀጥለን ደግሞ የምናየው በዓለ መስቀልን ለምን እንደምናከብር ነው።

የመስቀልን በዓል ለምን እናከብራለን?

የመስቀል በዓል የሚከበረው መስከረም 17 ቀን ነው። የሚከበርበትም ምክንያት፡- ጌታ በመስቀል ላይ ሙቶ ከተነሣ በኋላ ሕሙማን መስቀሉን እየዳሰሱ በመስቀሉ እየታሹ ይፈውሱ ነበር። ይህንን ያዩ አይሁድም በምቀኝነት መስቀሉን ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ ጣሉት። ከብዙ ጊዜም በኋላ ያ ቦታ እንደ ጉብታ ሆነ። ምንም እንኳ ለማውጣት ባይችሉ ክርስቲያኖቹ ያን ቦታ ያውቁት ነበር። በኋላ ግን በ70 ዓ.ም. በጥጦስ ወረራ ክርስቲያኖቹ ኢየሩሳሌምን ለቀው ስለወጡና የከተማዋም መልክ ስለተለወጠ መስቀሉ የተቀበረበትን ጉብታ ለማወቅ አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል ተዳፍኖ ቆይቷል። በኋላ ላይ ግን በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታላቁ ንጉሥ የቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ መስቀሉን ለማውጣት ብዙ ደከመች። በመጨረሻም ስሙ ኪርያኮስ የተባለ አረጋዊ በነገራት መሠረት ደመራ አስደምራ ዕጣን አፍስሳበት በእሳት ብትለኩሰው ጢሱ እንደ ቀስተ ደመና መስቀሉ ከተቀበረበት ጉብታ ላይ ተተክሎ በጣት ጠቅሶ የማሳየት ያህል አመልክቷታል። ሳትውል ሳታድር መስከረም 17 ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10 መስቀሉን አግኝታለች። ቅዳሴ ቤት /ቤተመቅደስ/ ተሠርቶ የተፈጸመው በመስከረም 17 ነው።  እንደወጣም ብዙ ተዓምራትን አድርጓል።

እንግዲህ በሀገራችን በኢትዮጵያ የመስቀልን በዓል ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት፥ ቅዳሴ በመቀደስና ማኅሌት በመቆም የምናከብረው ለዚህ ነው። በዚሁም ላይ ይህን ታላቅ ዕፀ መስቀል በወቅቱ የነበሩ ታላላቅ ነገሥታት የሚያደርጋቸውን ተዓምራት በማየት ለእያንዳንዳቸው ይደርሳቸው ዘንድ ከአራት ክፍል ሲከፍሉት ከአራቱ አንዱ የቀኝ እጁ ያረፈበት ግማድ /ክፋይ/ ብቻ በደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ሲገኝ ሌሎች ሦስቱ ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም። ይህም ግማደ መስቀል የመጣው በአፄ ዳዊት በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ የማስቀመጫ መቅደስ ለማሠራት መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አልረጋ ብሏቸው በርካታ አድባራትን ካዳረሱ በኋላም እግዚአብሔር “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል /መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ/” ብሎ ስለነገራቸው ተፈልጋ ግሸን ደብረ ከርቤ በተባለው ቦታ የመስቀል ቅርጽ ስለተገኘች ዛሬም ድረስ በዚሁ ታላቅ ቦታ ይገኛል። በዚህ ታላቅ ጸጋ የተጠቀሙት ብዙዎች ናቸውና እኛንም ከዚህ ረድኤት እንዲከፍለን በዓሉን በአግባቡና በሥርዓት ልናከብረው ያስፈልጋል። መልካም በዓል አክብረን የመስቀሉ ክብርና ጸጋ ረድኤት ይድረሰን። አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አዘጋጅ፡-
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን
የአሜሪካ ማዕከል የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል   
2006 ዓ.ም.