ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው?

፩. ሥርዓት ምንድን ነው?
 
ሥርዓት “ሠርዐ” ሠራ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ደንብ፣ አሠራር፣ መርሐ ግብር ማለት ነው። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስንልም የቤተ ክርስቲያን ዕቅድ፣ የቤተ ክርስቲያን አሠራር መርሐ ግብር ወይንም ደንብ ማለታችን ነው።
 
ሥርዓት የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፦
·        ሥራን ወጥ በሆነ መልኩ ለመፈጸም

ማንኛውንም ነገር ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራት ከየት ተጀምሮ በየት በኩል ሄዶ በየት በኩል እንደሚጠናቀቅ ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ይዘጋጅለታል። የአንድ ሥራ አሠራር በትክክል ካልተነደፈና አካሄዱ ካልተስተካከለ፤ ሥራው የተዘበራረቀ ይሆናል ፍጻሜውም አያምርም።

·        አንድ ሃሳብና አንድ ልብ ለመሆን

አንድ መሥሪያ ቤት በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ተግባብተውና ተረዳድተው እንዲሠሩ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል። ያ ሥርዓት ነው ሠራተኞቹን እንደመመሪያ ሆኖ ፈር እየቀደደ የሚመራቸውና የሚያስተዳድራቸው። ይህ ካልሆነ ግን እርስ በእርሷ እንደምትለያይ መንግሥት ሳይግባቡ ይቀሩና የመሥሪያ ቤቱንም ራዕይ ማሳካት ሳይችሉ ይቀራሉ። ለዚህ ነው በየአህጉራቱ፣ በየማኅበረሰቡ፣ በየማኅበሩ፣ በየቤተሰቡ የመተዳደሪያ ሥርዓት ማውጣት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የሆነው። እንደውም አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ሊኖራቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል ሥርዓት አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ሲነገር ሁላችንም እንሰማለን።

ማኅበረ ምዕመናንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ አንድ ዓይነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገናል። ብዙ ስንሆን አንድ ልቡና አንድ ሃሳብ የሚያደርገን ሥርዓት ነውና። /ኤፌ. ፬፥፫፤ የሐዋ. ፬፥፴፪፤ ሮሜ. ፲፭፥፮/።

·        የሃይማኖትን ምሥጢራት ለመጠበቅ
ሥርዓት የሃይማኖት መገለጫ ነው። ጥምቀት፣ ቁርባን፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ሥግደት፣ ወዘተ በማመን ብቻ የሚያበቁ ሳይሆን የአፈጻጸምና አተገባበር መንገድ /ሥርዓት/ ያስፈልጋቸዋል። የእነዚህ ሁሉ ዝርዝር አፈጻጸም በሥርዓት ውስጥ ይካተታል። ስለዚህ በአንዲት ርትዕትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት ሥር ያሉ ሁሉ ያቺን አንዲት እምነት የሚገልጹት አንድ ዓይነት በሆነ ሥርዓት ነው። ሥርዓት በመሠረተ እምነት /ዶግማ/ የምናምናቸውን በተግባር የምንገልጽበትና ተግባራዊ የምናደርግበት መንገድ ስለሆነ ሥርዓቱ ሲሠራና ሲፈጸም ሃይማኖታዊ አንድምታና ነጸብራቅ ይኖረዋል።
  
፪. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
ቤተ ክርስቲያን ማለት ሕንፃው፣ የክርስቲያኖች አንድነት /ጉባኤ/ እና የምዕመኑ ሰውነት በመሆኑ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የምንለውም በእነዚህ በሦስቱ ላይ የተሠራውን ሥርዓት ነው። አንዳንዶቻችን ቤተ ክርስቲያንን ከራሳችን አርቀን ሌላ አካል አድርገን ስለምንመለከት ሥርዓቱ እኛን የሚመለከት አይመስለንም። ሥርዓቱ ግን የተሠራው ለሦስቱም የቤተ ክርስቲያን ትርጓሜዎች መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።
ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንጩ ወይንም መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የቅዱሳን አባቶቻችን ጉባኤያት ውሳኔ /ሲኖዶስ/ እና አባቶቻችን ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜ ያደረጓቸው ጉባኤያት ውሳኔዎች ናቸው።
ሰንበትን ማክበር፣ በጻድቃን ስም አብያተ ክርስቲያናትን ማነጽ፣ የቁርባን ሥርዓት፣ የመሳሰሉት ከመጽሕፍ ቅዱስ የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው። /ዘፍ. ፳፰፥፳-፳፪፤ ዘጸ. ፲፮፥፳፱፤ የሐዋ. ፩፥፲፪/።

ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባውንና የተቀደሰውን ንዋየ ቅድሳት እንደገና ወደውጭ አውጥቶ ለሥጋዊ ጥቅም ማዋል እንደማይገባ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩ ረስጣ ፳፰/፣ ጥምቀት በፈሳሽ ውኃ መፈጸም እንዳለበት፣ ወንዶች ሴቶችን ሴቶች ደግሞ ወንዶችን ክርስትና እንዳያነሱ፣ ሥጋ ወደሙ ለመቀበል ፲፰ ሰዓት መጾም እንደሚገባ፣ ሥጋ ወደሙ በምድር ላይ እንዳይወድቅ /እንዳይነጥብ/፣ ያላመኑ ሰዎች ሥጋ ወደሙን መቀበል እንደሌለባቸው፣ ወዘተ ያሉት ደግሞ በሲኖዶስ /የቅዱሳን አባቶቻችን ጉባኤያት/ የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው።

ከእናቱ፣ ከእህቱ፣ ከአክስቱ ወይንም እንደዚህ ባለ ሁኔታ ከምትታሰብ ሴት ጋር ካልሆነ በቀር አንድ ኤጲስ ቆጶስ፣ አንድ ቄስ፣ አንድ ዲያቆን፣ ወይንም ሌላ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከማንኛውም ሴት ጋር አብሮ እንዳይኖር፤ ስለ መናፍቃን ጥምቀት፣ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር፣ ስለ ድንግልና ኑሮ፣ ወዘተ ደግሞ በተለያዩ ጉባኤያት አባቶቻችን ያስተላለፏቸው ውሳኔዎችና ቀኖናዎች የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው።

የቤተ ክርስቲያን አመሰራረትና የቅዳሴ አገልግሎት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር
 
መቼም በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እየሰፋች ከሀገር ቤት አልፋ በውጭ ሀገርም አብያተ ክርስቲያናት እየታነጹ ስለሆነና ሁላችንም የቻልን ዘወትር ቅዳሴ በሚቀደስባቸው ዕለታት፣ ያልቻልን ደግሞ በዕለተ ሰንበት ለቅዳሴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለምንሄድ ስለ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት፣ አሠራርና ቡራኬ፣ እንዲሁም ስለ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዴት መሆን እንዳለበት እንገነዘባለን። ለዚህም እንዲረዳን እንደሚከተለው እናያለን።
 

ቤተ ክርስቲያን ስትሠራ

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ቃሉ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል /ቤቴሰ ቤተጸሎት ትሰመይ/ የሚለው /ኢሳ. ፶፮፥፮-፯፤ ኤር. ፯፥፲፩፤ ማቴ. ፳፩፥፲፫፤ ማር.  ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፮፤ ዮሐ. ፪፥፲፮-፲፯/ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን የዋዛ የፈዛዛ፣ የሳቅ የስላቅ፣ የጨዋታ፣ የመብል፣ የመጠጥ ቤት ሳትሆን፤ ምዕመናን ኃጢአት ቢሠሩ ሰለ ኃጢአታቸው የሚያዝኑባት የሚያለቅሱባት ንጹሕ የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ካህናት የሚያስተምሩባት፣ ምዕመናን የሚማሩባት የግል ጸሎት፣ የማኅበር ጸሎት የሚጸልዩባት፣ በኅብረት የሚያስቀድሱባት ሥጋ  ወደሙ የሚቀበሉባት፣ የኃጢአት ሥርየት የሚያገኙባት፣ ሕፃናት በአርባ ቀንና በሰማንያ ቀን በጥምቀተ ክርስትና አማካኝነት ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት የሚቀበሉባት፣ ኢአማንያን የነበሩ በመምህራን ትምህርት አምነው ክርስቲያን የሚሆኑባት፣ ለክህነትም ሆነ ለአባልነት የዘር ሐረግ የማይቆጠርባት ዓለም አቀፋዊት የእግዚአብሔር ቤት ናት፡፡
 
አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስትመሠረት ጀምሮ ሥርዓት አላት። የምትመሠረተው ባንድ ግለሰብ ስም ሳይሆን በካህናትና በምዕመናን ጥያቄ በሀገረ ስብከቱ ኤጲስ ቆጶስ ፈቃድና ትእዛዝ ነው፤ ካለኤጲስ ቆጶስ ፈቃድ ከመጽሐፉ ትዕዛዝ ወጥቶ አንዱ ቢያቋቁም ወይም ቢሠራ ቤተ ክርስቲያን ናት ብለው ለዘለዓለሙ በዛች ቤተ ክርስቲያን አይቁረቡባት፤ እንደገበያ፣ እንደእንስሳት በረት ፈት ሆና ትኑር ይላል። /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩-፫/።
 
ቤተክርስቲያን ለመሥራት ፈቃድ ከተገኘ በኋላ ስለ አሠራሯ የሚከተለው ሥርዓት ተሠርቶላታል። ቤተ ክርስቲያኗ ስትሠራ ደጆችና መስኮቶች አውጡላት ዛፍ ቅረጹላት ሐረግ ሳቡላት እንደሚል በተቻለ መጠን ሊያስጌጧት ይገባል የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናትና።  በሰማይ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት እንዲያበሩ፣ ሰባቱ ሰማያት ብሩሃን እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያንም ብርህት ትሁን፤ ይልቁንም ክቡራት መጻሕፍት ሐዲሳት፣ የጳውሎስ መልእክታት፣ የሐዋርያት መልእክታት፣ ግብረ ሐዋርያት በሚነበቡበት ጊዜ የበራች ትሁን፣ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ያለውም ይህንኑ ያመለክታል። /ማቴ. ፭፥፲፬/። ቅዱስ ወንጌል በሚነበብበት ጊዜ ግን ፈጽማ የበራች ትሁን፤ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ያለው ይሻል። /ዮሐ. ፱፥፭/።
 
ቤተ ክርስቲያን ስትባረክ
 
ቤተ ክርስቲያን ሕንፃዋ ተፈጽሞ በምትባረክበትና በምትቀደስበት ጊዜ ከኤጲስ ቆጶሱ ጋር ሰባት ቀሳውስት አብረውት ሊኖሩ ይገባል፣ ታቦቱም በሚባረክበት እንደዚሁ ሊሆን ይገባል፣ ኤጲስ ቆጶሱ እግዚአብሔር ሰውን የሚያከብርበት ራሱን የሚያስመስልበት ነውና ደስ በሚያሰኝ በቅብዐ ቅዱስ በሜሮን ያክብራት ያትማት፣ ታቦቱንም በመቅደስ ውስጥ በመንበር ያስቀምጡባት ከታቦቱ ጋራ የዮሐንስን ወንጌል ያኑሩ ከደቀ መዛሙርቱም በጌታ ኢየሱስ አጠገብ የሚቀመጥ ጌታ የሚወደው ቅዱስ ዮሐንስን ነበርና። /ዮሐ. ፲፫፥፳፫/ ።
 
ታቦቱም ሲቀረጽ ከላይ አልፋ፣ ቤጣ፣ የውጣ፣ ወኦ/ወዖ/ ይቀረጻል። ቀጥሎ እመቤታችንን፣ ከእመቤታችን ቀጥሎ ዮሐንስን፣ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያኑ የሚተከለው ታቦት መልአክም ቢሆን፣ ሰማዕትም ቢሆን፣ ጻድቅም ቢሆን ይቀረጻል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ካልተሟሉ ታቦቱን ሊቀድሱበት አይገባም።
 
ከቤተ ክርስቲያን የገባ ዕቃ የወርቅ፣ የብር፣ ፃሕል ጽዋእ እርፈ መስቀል ቢሆን ንዋየ ቅድሳት ነው ተብሎ አቡነ ዘበሰማያት ከተደገመበት በኋላ ከቤታቸው ወስደው በፃሕሉ ፈትፍተው ሊበሉበት በጽዋው ቀድተው ሊጠጡበት አይገባም። ደፍረው ቢያደርጉ ሥርዓት ማፍረስ ነውና ይህን ያደረገ ቢኖር በአንድ ሁለት ተቀጥቶ ንሰሐውን እሰኪፈጽም ከምዕመናን ይለይ። /ዳን. ፭፥፩-፴፩/።
 
በቤተ ክርስቲያንም ኤጲስ ቆጶሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ምዕመናን እንዴት መቆም እንዳለባቸው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ይገልጻል። ኤጲስ ቆጶሳት የቤተ ክርስቲያን አዛዚያን እንደመሆናቸው በታቦቱ ፊት ይቁሙ፣ ቀሳውስትም መምህራን እንደመሆናቸው ከኤጲስ ቆጶሳት ቀጥለው ይቁሙ፣ ሊቀ ዲያቆናትም ከኤጲስ ቆጶስ አጠገብ ይቁሙ፣ ዲያቆናትም አገልጋዮች እንደመሆናቸው ከቀሳውስት ቀጥለው ይቁሙ፣ ከዲያቆናት ቀጥለው ሕዝቡ ሁሉ ባንድ ቦታ ይቁሙ፣ የሚበቃ ቦታ ቢኖር ሕፃናት በአንድ ወገን ለብቻቸው ይቁሙ፣ የሚበቃ ቦታ ከሌለ ግን ከአባቶቻቸው ጋራ ተስገው ይቁሙ፣ እንደዚሁም ሴቶች ባንድ ወገን /ቦታ/ ለብቻቸው ይቁሙ፣ ቦታ ቢገኝ ሕፃናት ሴቶች ባንድ ወገን ለብቻቸው ይቁሙ፣ ቦታ ባይኖር ግን ሕፃናቱ በፊት እናቶች በኋላ ይቁሙ፣ ደናግላን ሴቶችና ባልቴቶች ግን ከሴቶች በላይ ይቀመጡ ። /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፪ ድስቅ ፲፪ ኒቅያ ፷፩/።
 
ሥርዓተ ቅዳሴ
 
በቅዳሴ ጊዜ ስለሚደረጉና ሰለማይደረጉ ነገሮች ደግሞ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ያዝዛል፦
 
በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ሰው ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው በ፸፪ኛው አንቀጽ ካህን ቢሆን የሚያቀብል ነውና ሥጋ ወደሙን ከተቀበለና ካቀበለ በኋላ ወጥቶ አንድ ሱባዔ ይቀጣ ይጹም ይስገድ፣ የሳቀው ሕዝባዊ ቢሆን ግን ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል ያን ጊዜ ፈጥኖ ይውጣ ይላል። ምነው ፍርድ አበላለጠ ካህኑን ተቀብሎ ወጥቶ ይቀጣ አለ፤ ሕዝባዊውን ሳይቀበል ወጥቶ ይሂድ አለ ቢሉ ካህኑ የሚቆመው ከውስጥ ነው ሲስቅ የሚያየው የለም። ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ ቅዳሴውን ጥሎ ወጥቶ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ቄስ እገሌ አባ እገሌ በመሥዋዕቱ ምን አይተውበታል ብለው መሥዋዕቱን ሳይቀር ይጠራጠሩታል፤ ስለዚህ ነው። ምዕመኑ ግን ሲስቅ ሁሉ ያየዋልና ለሌላ መቀጣጫ እንዲሆን፤ በቤተ መቅደስ የማይወደድ ሌላ ነገር አይናገር፤ በቤተ መቅደስ ጭንቅ፣ ደዌ ሳያገኘው አንዱን ስንኳ ምራቁን እንትፍ አይበል። ነገር ግን ደዌ ቢያስጨንቀው ድምፅ ሳያሰማ ምራቁን በመሐረቡ ተቀብሎ ያሽሸው።
 
በቤተ ክርስቲያንና በቅዳሴ ጊዜ ማንም ማን ዋዛ ፈዛዛ ነገር የሚናገር አይኑር፣ ቤተ ክርስቲያን በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነው የሚጸልዩባት የጸሎት ቦታ ናትና ቅዳሴው ሳይፈጸም አቋርጦ መውጣት አይቻልም፣ አይፈቀድም፣ በጣም ጭንቅ ምክንያት ወይም በሕመም ምክንያት ከሆን ግን ክቡር ወንጌል ከተነበበ በኋላ ሊወጣ ይችላል። በቅዳሴ ጊዜ ካህናት የሚቀድሱባቸው አልባሳት ነጫጭ ይሁን ነጭ ልብስ ደስ እንዲያሰኝ በሥጋ ወደሙ የተገኘ ክብርም ደስ ያሰኛልና፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ባህርየ መለኮቱን በገለጸ ጊዜ ልብሱ እንደበረድ ነጭ ሆኗል። መላእክትም ወርኃ ሰላም ወርኃ ፍስሐ ነው ሲሉ የልደት፣ የትንሣኤ፣ የዕርገት ነጫጭ ልብስ ለብሰው ታይተዋል።
 
አንድ ሰው እንኳ ጫማ አድርጎ ከቤተ መቅደስ አይግባ ልዑል እግዚአብሔር የምትቆምባት ደብረ ሲና የከበረች ናትና ጫማህን አውልቅ ብሎ ለሙሴ ተነግሮታልና። /ዘጸአት ፫-፭/ ።
 
በቅዳሴ ጊዜ ተሰጥዖውን የማያውቅ ደግሞ በአንክሮ፣ በተዘክሮ፣ በአንቃእድዎ፣ በንጹሕ ልቡና፣ በሰቂለ ሕሊና ሆኖ ሕሊናው ወደ ዓለማዊ እንዳይወስደው መቆጣጠር አለበት።
 
ቅዱስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ካህኑ ለሕዝቡ ተርጉሞ ይንገራቸው ያስተምራቸው እጁንም በሚታጠብበት ጊዜ የተጣላችሁ ሳትታረቁ፣ የሰው ገንዘብ የወሰዳችሁትን ሳትመልሱ ሥጋ ወደሙን ብትቀበሉ ሥጋው እሳት ሆኖ ይፈጃችኋል ደሙ ባህር ሆኖ ያሰጥማችኋል። ነገር ግን የወሰዳችሁትን የሰው ገንዘብ መልሳችሁ፣ ከተጣላችሁት ታርቃችሁ ኃጢአት ብትሰሩ ንስሐ ገብታችሁ ብትቀበሉት ግን መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ይሆናችኋል። በረከተ ሥጋውን በረከተ ነፍሱን ያድላችኋል ብሎ ይንገራቸው ያስተምራቸው ይላል።
 
በቅዱስ ቁርባን ጊዜም አስቀድሞ ሊቃነጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ በቁምስና መዓርግ ያሉ መነኮሳት፣ ቀጥሎ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ ወንዶች በአርባ ቀን የሚጠመቁ ሕፃናት ከሁሉ አስቀድመው ይቀበሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና። ከነዚህ ቀጥሎ ከአርባ ቀን በኋላ እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉት ሕፃናት ትንሾቹ በፊት እየሆኑ እንደየዕድሜያቸው ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው /ክህነት የሌላቸው/ በድንግልና ኑረው የመነኮሱ ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ሃያ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆናቸው ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው በሹመት ያሉ ናቸውና ንፍቀ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢሳውያን፣ መዘምራን ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።
 
በሴቶችም በኩል ከሁሉ አስቀድሞ የተጠመቁ የሰማንያ ቀን ሕፃናት ይቀበላሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና፤ ከነዚያ ቀጥሎ ከሰማንያ ቀን እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናት እንደየዕድሜያቸው ሕፃናቱ አስቀድመው ታላላቆች ቀጥለው ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው አሥራ ሁለት፣ አሥራ አምስት የሆናቸው ደናግል ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የቀሳውስት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ኑረው የመነኮሱ እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያው ቀጥለው የዲያቆናት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በንሰሐ ተመልሰው የመነኮሱ መነኮሳት እና መነኮሳይያትይቀበላሉ፤ ከነዚያ በኋላ የንፍቀ ዲያቆናት፣ የአናጉንስጢሳውያን፣ የመዘምራን ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ጸንተው ያሉ ሕጋውያን እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን ሚስቶች በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።
 
ከዚህ በኋላ ካህኑ ሥጋ ወደሙን በፈተተበት እጁ ሕዝቡን ፊታቸውን ይባርካቸው። ቀሳውስት ግን እጅ በእጅ ተያይዘው እርስ በርሳቸው ይባረኩ። ቀዳሹ ካህን ቀሳውስትን ሲያሳልም “የጴጥሮስን ሥልጣን ባንተ አለ” ይበል፣ ተሳላሚው ቄስም “መንግሥተ ሰማያት ያውርስህ ከሾመ አይሻርህ” ይበል። ለዲያቆናትም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ ይባርክህ፣ ለማስተማር ዓይነ ልቡናህን ያብራልህ፣ ምሥጢሩን ይግለጥልህ” እያለ ይባርካቸው። ለምዕመናንም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ይባርክህ፣ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልህ” እያለ ይባርካቸው። ለሴቶችም “ልዑል እግዚአብሔር ይባርክሽ፣ ያክብርሽ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልሽ” ብሎ በእጁ ይባርክ።
 
 
 ይቆየን !
 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር