ሰንበት ዘብርሃን

ሰንበት ዘብርሃን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ነአምን ክልኤተ ልደታተ እንዳሉ አባቶቻችን በሃይማኖተ አበው፤ ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት፣ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ፣ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የአብ አካላዊ ቃል ፤ ድኀረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት፣ መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን፣ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነ ፤ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትስብእቱ ፤ የሚባል ጌታ በተዋሕዶ ከበረ ብለን የቀናች የአባቶቻችን ሃይማኖታቸው ተዋሕዶን እንመሰክራለን፡፡

ስንዱዋ እመቤት ቤተክርስቲያናችን ወራትን እና ዘመናትን ከፍላ ነገረ ሃይማኖትን ታስተምራለች።አባቶቻችንም የወራቱንና የቀናቱን  የሰንበታቱንም ምስጢር በማገናዘብ የመጽሐፍ ቅዱስን ምንባባት ከቅዱስ ያሬድ መዝሙር ጋር በማዛመድ ግጻዌ የሚባልን መጽሐፍ ሰርተውልናል።

መዝሙር ዘብርሃን

በግጻዌ ዘሰናብት ከታኅሣሥ ፲፬  እስከ ታኅሣሥ ፳  ባሉት ቀናት ውስጥ ያለውን ሰንበት ብርሃን እንደሚባልና መዝሙሩም “ዘብርሃን አቅዲሙ ነገረ በኦሪት”የሚለው እንደሆነ አባቶቻችን ሠርተውልናል፡፡

ይህም የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ነገረ ሥጋዌን ነገረ ድኅነትን በውስጡ የያዘ ነው። ቅዱስ ያሬድ እንደ ንብ ነው፤ንብ ከመልካም አበባ ሁሉ እንዲቀስም ቅዱስ ያሬድም ከኦሪቱ ከነቢያቱ ከሐዲሳቱ እየጠቀሰ መጥኖ ማር የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር አዘጋጅቶልናል፡፡

“ዘብርሃን አቅዲሙ ነገረ በኦሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሐት ዘይዜንዋ ለጽዮን ቃለ ትፍሥሕት”

ቃለ ትፍሥሕት የደስታ ቃልን አንድም ደስ የሚያሰኝ የምስጋና ቃልን፣ ለጽዮን ለሕዝበ ፳ኤል  የሚነግራት፣ ወልድ በክብር በምስጋና ለተዋሕዶ ለድኅነተ ዓለም ፣ ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ  አስቀድሞ በኦሪት ተነገረ ይለናል ሊቁ ቅዱስ ያሬድ፡፡

አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው እንደሚሆንና እኛን እንደሚያድነን አስቀድሞ በኦሪት የተነገረውን ሲያስታውሰን ነው ፡፡ ለአብነትም  “አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንዳንዱ ሆነ” ዘፍ  ፫፥፳፪ ተብሎ የተነገረው የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን የሚያሳይ ነው፡፡

“ወካዕበ ይቤ በአፈ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ”

ዳግመኛ ምስክርነቱ የታመነ አምላክ እንደልቤ ብሎ ባከበረው በቅዱስ ዳዊት አንደበት “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” መዝ ፻፲፯፥፳፮ አለ ይለናል ሊቁ  ቅዱስ ያሬድ፡፡ በስመ እግዚአብሔር፦ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእግዚአብሔር ስም ፤በስምዐ እግዚአብሔር፦ እግዚአብሔር አብ መስክሮለት የመጣ ወልደ እግዚአብሔር ጌታ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትን በአፈ ዳዊት እያለ ትንቢቱን ምስክርነቱን ያነሳዋል ፡፡ አባቶቻችንም ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን ያለውን ፲፬ ትውልድ በሰንበት ዘብርሃን ያስቡታል፡፡

“ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም ዘያበርህ ላዕለ ጻድቃን”

ቅዱስ ያሬድ ወልደ እግዚአብሔርን ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም የመጣው ብርሃን ዘበአማን፤  የዚህ ዓለም ጠፈር ደፈር የማይከለክለው መዓልትና ሌሊት የማይፈራረቅበት እውነተኛ ብርሃን፤ ለጻድቃን የሚያበራ ብሎ ይገልጠዋል፡፡ ይህም ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌል የመሰከረው ሊቃውንቱ እነ ቅዱስ ኤፍሬም በእመቤታችን ውዳሴ ላይ ያመሰጠሩት ነው፡፡

“መርዓዊሃ ለቤተ ክርስቲያን”

ቅዱስ ያሬድ ወልደ እግዚአብሔርን የቤተክርስቲያን ሙሽራ ብሎ ይገልጠዋል፡፡አካል የሌለው ራስ እንደሌለ ፥ ሙሽሪት የሌለችውም ሙሽራ የለም ። አካል፥ ሙሽሪት ያላት ቤተክርስቲያንን ሲሆን ራስ፥ ሙሽራ የተባለው ደግሞ ክርስቶስ ነው።ይህንም ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና” ብሎ ገልጦታል ኤፌ ፭፥፳፫

“ይርዳእ ዘተኀጒለ ያስተጋብእ ዝርዋነ መጽአ ኀቤነ”

ከ፻ በጎች መካከል የጠፋውን አዳምንና ልጆቹን ይረዳ ይፈልግ ዘንድ፣ የተበተኑትን ይሰበስብ ዘንድ ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም ወደ እኛ መጣ ፡፡

ምስባክ ዘብርሃን መዝ ፵፪፥፫


‹‹ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ

እማንቱ ይምርሓኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ

ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ  ››

 

ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ

 

  • (ብርሃነከ) ብርሃን የተባለ ወልድን (ወጽድቅከ) መንፈስቅዱስን ላክልኝ
  • ብርሃነ ረድኤትህን አንድም ዮሴዕ ዘሩባቤልን ቂሮስ ዳርዮስን ላክልኝ
  • (ብርሃነከ) ሐዋርያትን (ወጽድቅከ) ሰብአ አርድእትን ላክልኝ
  • (ብርሃነከ) መስቀልን (ወጽድቅከ) ቀኖትን  ላክልኝ
  • (ብርሃነከ) ሥጋውን (ወጽድቅከ) ደሙን ላክልኝ

 

እማንቱ ይምርሓኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ

 

ብርሃን  የተባለ ወልደ እግዚአብሔርን በሐዋርያት በሰብአ አርድእት ትምህርት አምነን ሥጋውን ደሙን ተቀብለን መከራ መስቀሉን አስበን ወደመንግስቱ እንገባለንና እሊህ መርተው መመስገኛህ ወደምትሆን ወደ ኢየሩሳሌም ይውሰዱኝ ዘንድ ይላል ኅሩይ ቅዱስ ዳዊት


ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ

እነሱ መርተው ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ያግቡኝ።አብያት ብሎ መንግስተ ሰማያትን በብዙ ቁጥር ይናገራል።በብዙ ወገን በድንግልና፣ በሰማዕትነት፣ በብሕትውና አንድም በብዙ ማዕረግ በ፴፣ በ፷፣ በ፻ የምትወረስ ስለሆነ ነው።አንድም በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ እንዳለው በብዙ ተናገረ

በብርሃን የሚነበቡ ምንባባት

 

በሰንበት ዘብርሃን የሚነበቡ ምንባባት በዕለቱ መዝሙር ‹‹ዘብርሃን አቅዲሙ ነገረ በኦሪት›› ብርሃን ዘበአማን የተባለው እውነተኛው የዓለም ብርሃን ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ በኦሪት በነቢያት አስቀድሞ መነገሩን የሚያበስሩ የልደተ ክርስቶስን ዋዜማ የሚያስታውሱ ናቸው

 

    • ሮሜ  ፲፫ ፲፩ ፡ ፲፬ ‹‹ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና።ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ።በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ።….››

 

  • ፩ኛ ዮሐ ፩ ፥ ፩፡፲ ‹ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።››
  • የሐዋ ፳፮ ፥፲፪ ፡ ፲፱ ‹‹ስለዚህም ነገር ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥ንጉሥ ሆይ፥ በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ

 

ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ።እኔም  ጌታ ሆይ፥ ማንነህ አልሁ እርሱም አለኝ። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ።ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና።የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም››

 

ወንጌል ዘብርሃን ዮሐ ፩፥፩ – ፲፱



‹‹በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።

ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።

ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።አይሁድም አንተ ማን ነህ ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው››

 

በትርጓሜ ወንጌል አባቶቻችን ይህን ስለ መለኮታዊ የሕይወት ቃልና ስለ ዮሐንስ መላክ የሚያትተውን ምንባብ በሰፊው አምልተው አመስጥረው ጽፈው አስቀምጠውልናል።

  • በቅድምና ስለነበረው ቃል ሲያብራሩ፦ ተጠመቀ ለማለት ተወለደ ማለት ጥንቱ ነው፤ተወለደ ለማለት ተፀነሰ ማለት ጥንቱ ነው፤ተፀነሰ ለማለት በቅድምና ነበረ ማለት ጥንቱ ነው።ያ ቃል ከስነፍጥረት አስቀድሞ የነበረ እግዚአብሔር ወልድ እንደሆነ ሲያስረዳም ያም ቃል ስጋ ሆነ ብሎ ያመጣዋል።ልብ እስትንፍስ ቀድመውት ወደኋላ የሚገኝ ቃል የለምና ቅድስት ሥላሴ አባት በመሆን አብ ወልድን አይቅድመውም አይበልጠውም፤ ወልድም መንፈስቅዱስን አይበልጠውም አይቀድመውም ፤ሦስቱ ስም አንዱ እግዚአብሔር ነው ብሎ አባ ሕርያቆስ እንደተናገረ አሐቲ ቅድምናሆሙ ለሥላሴ ወዕሩያን እሙንቱ በቅድምና እንዲል የቅድስት ሥላሴ ቅድምና አንድ የሆነ የተካከለ ቅድምና ነው።
  • ስለ ዮሐንስ መላክ ሲያብራሩ፦መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የብርሃንን ነገር ይመሰክር ዘንድ የመጣ እንጂ እራሱ ብርሃን አይደለም፤ሰው ሁሉ ብርሃን በተባለ ክርስቶስ ያምን ዘንድ የሚናገር፤በጨለማ በድንቁርና፣ በቀቢጽ ተስፋ በሞት ጥላ ውስጥ ሁሉ ለሚኖር ዓለም ፣ ዕውቀትን የሚገልጥ ጨለማን የሚያርቅ፣ ምትን ድል አድርጎ ተስፋ መንግስተ ሰማያትን የሚሰጥ  መሆኑን መስክሯል።

 

ማቴ ፭፥፲፮ ‹‹መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ››በጎ ሥራችሁን አይተው ሰማያዊ አባታችሁን እንደነርሱ  አርአያ የሚሆኑ የትሩፋት አበጋዝ ያስነሳልን አምላካችን ብለው እንዲያመሰግኑት ብርሃን በጎ ሥራችሁ ይገለጥ ብሎ ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል።ብርሃን ዘበአማን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ዕውቀትን በጎ ምግባርን ያድለን በብርሃን የምንመላለስ የብርሃን ልጆች ያድርገን  ወንድማችን የምናሰናክል ሳይሆን ለሌላው አርአያ የምንሆን ያድርገን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በኩረ ፍሥሐ ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን