ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና ታሪካዊ አመጣጣቸው
ዲያቆን ተመስገን ዘገየ
ከትንሣኤ ሌሊት ፩ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያለው ሳምንት የፉሲካ ምሥጢር የተገለጠበት፤ ከግብፅ ወደ ምድረርስት ከሲኦል ወደ ገነት መሻገርን የሚያመላክት ሳምንት ነው። ለፉሲካ የሚታረደውም በግ ፉሲካ ይባላል (ዘዳ. ፲፮÷፪:፭÷፮)፤ ፉሲካ ማለት ደግሞ ማለፍ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትም ሳምንት የፉሲካ ሳምንት ነበር፤ (ሉቃ. ፳፪፥፲፬-፲፮፤ ዮሐ. ፲፰፥፴፰-፵)።
እርሱም ንጹሕ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን ፉሲካችን ክርስቶስ ተባለ፤ ብሉይ ደግሞ የሐዲስ አምሳል ነው። ይኸውም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ባሕረ ኤርትራን ካሻገራቸው በኋላ ወደ ምድረ ርስት፤ ነፍሳት ደግሞ በክርስቶስ መሪነት ከሲኦል ወደ ገነት መግባታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ዕለቱም ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፤ በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌ፤ግብፅ የሲኦል፤ የገሃነመ እሳት፤ የፈርዖን የዲያብሎስ፤ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ፤ እስራኤል የምእመናንና ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል ምሳሌ ነው፡፡
ሰኞ– ማዕዶት (ፀአተ ሲኦል)
ማዕዶት የቃሉ ትርጓሜ መሻገር ሲሆን፤ በዚህ ቀን ቤተ ክርስቲያን ነፍሳት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሐሳር ወደ ክብር፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት መሻገራቸውንና ፉሲካችን ክርስቶስ መሆኑን ታስባለች።
ማክሰኞ– ቶማስ
ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን፤ በቀኖት የተቸነከረው እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስም «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን» ብሎታል። ቶማስም «ጌታዬ አምላኬም»፤ ብሎ በመለሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስም «ስለ አየኸኝ አመንህን? ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓንስ ናቸው» አለው (ዮሐ ፳፥፳፯-፳፱)፤ ቶማስ የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን ስላመነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን ቶማስ ብላ ታስበዋለች።
ዲዲሞስ የተባለ ከአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙር አንዱ ቶማስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝግ ቤት ገብቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ባላቸው ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ አልነበረም»። ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ (ማቴ. ፲፥፪-፫) ቶማስ በአራማይክ ዲዲሞስ በግሪክ መንታ ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፳፥፳፬)፡፡ ቶማስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በፋርስና በሕንድ ወንጌልን እንዳስተማረ ይነገራል። ለቶማስ ጎኑን እንዲዳስስ የፈቀደው ለሌሎችም ቅዱሳን ሐዋርያት የተቸነከረውን እጅና እግሩን ያሳየው ካህናት ሥጋውና ደሙን እንዲፈትቱ ነው፤ ዮሐንስም በእጃችን ዳሰስነው ብሏል፤ (ሉቃ. ፳፬፥፴፱)፡፡
ለማርያም መግደላዊት ግን የተነሣ ዕለት አትንኪኝ ማለቱ ለሴቶች ሥጋውን ደሙን መፈተት አልተፈቀደም ሲል ነው ብለው ሊቃውንት ያትታሉ፤ «አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጅና፡- ወደ አባቴ÷ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ÷ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው» አላት፤ (ዮሐ. ፳፥፲፯)። ገቦ መለኮቱን የዳሰሰች እጁ በሕይወት ትኖራለች፤ በሕንድ ሀገር ከታቦት ጋር በመንበር ላይ ትኖራለች። በየዓመቱ በእመቤታችን በዓል በአስተርእዮ ሊያጥኑ ሲገቡ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች፤ ዓመት አገልግሎ ያርፋል።
ረቡዕ –አልዓዛር
አልዓዛር ክርስቶስ ያስነሣው የማርያምና የማርታ ወንድም ነው፤ የስሙም ትርጓሜ እግዚአብሔር ረድቷል ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፲፩፥፯-፵፰)፤ አልዓዛር የሞተው መጋቢት ፲፯ ነበር፡፡ እህቶቹም ክርስቶስ እንዲመጣ መልእክት ልከውበት ነበር፤ ክርስቶስ ግን በ፬ኛው ቀን ማለትም መጋቢት ፳ መጥቶ ከሞት አስነሥቶታል፤(ዮሐ.፲፩፥፵፬)፡፡ ፋሲካውንም በወዳጁ በአልዓዛር ቤት ያከብር ዘንድ ከቀደ መዛሙርቱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አስቀድሞ ላከ፤ ከዚያም በአልዓዛር ቤት ሆኖ የሐዲስ ኪዳንን ሥርዓት ምሥጢረ ቁርባንን ሰርቶ ለደቀ መዛሙርቱ አሳያቸው፤ አልዓዛር ከተነሣ በኋላ በሐዋርያት ኤጲስ ቆጶስነት ተሸሞ ፵ ዓመት አገልግሎ ግንቦት ፳፯ ቀን ዐርፏል (ስንክሳር ግንቦት ፳፯)፡፡
አዳም ሐሙስ
አዳም የመጀመሪያ ሰውና የሰው ሁሉ አባት ነው፤ በ፮ኛው ቀን የተፈጠረ የሰው ሁሉ ምንጭ ስለሆነ የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ፤ (ዘፍ. ፫÷፲፭) አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብበታል፡፡ ክርስቶስ በተነሳበት በአምስተኛው ቀን ሐሙስ አዳም ይባላል፤ ጌታችን አዳምን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ቃል ገብቶለት እንደነበር በቀሌምንጦስ ተጽፏል፡፡
አዳምና ሔዋን በገነት ፯ ዓመት ከቆዩ በኋላ ትእዛዙን በመተላለፋቸው ከኤደን ገነት አስወጣቸው (ኩፋ.፬፥፲፮፤ዘፍ.፫፥፳፫) «ብዙ ተባዙ» ያለው ቃል እንዳይቀር በምድር ላይ ወርደው ልጆችን ወለዱ ይላል፡፡ የተወለዱትም ልጆችም በቁጥር ፷ እንደሆኑ (፩መቃ. ፳፰፥፮) የተወለዱት ልጆች ደጎችና ክፉዎች እንደ ነበሩ በአቤልና በቃየል ታውቋል፤ (ዘፍ. ፬፥፰)፤ አዳም በዚህ ዓለም ፱፻፴ ዓመት ኑሮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፵፻፭፻፸ ሚያዚያ ፮ ዐርፏል፡፡
ዐርብ– ቤተ ክርስቲያን
ዐርብ የእግዚአብሔር ቅድስት ማደሪያ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ተሰይማለች፤ ይህም ሁሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ ነው፤ ዕለተ ዐርብ፤ የሥራ መከተቻ፤ ምዕራብና መግቢያ በሚሉት ስያሜዎችም ትጠራለች፡፡
በዕለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ያደረገውን ተአምር በመስቀሉ ድኅነትን እንዳሳየ፤ በቀራንዮ የሕንጻዋ መሠረት እንደተተከለላትና ሥጋ መለኮት እንደተቆረሰላት፤ ልጆቿን ከማሕፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ እንደፈሰሰላት ተገልጾባታል፤(ኤፍ.፪፥፲፱፤ራዕ.፩፥፮-፰)፡፡
ቅዳሜ– ቅዱሳት አንስት
ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፤ ይህም ስያሜ በስቅለት ዕለት በልቅሶና በዋይታ የሸኙትን፤(ሉቃ. ፳፫፥፳፯) በዕለተ ትንሣኤ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፤«ከሳንምንቱ በመጀመሪያዩቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ (ሉቃ. ፳፬ ፥ ፩ )፡፡
እሑድ– ዳግም ትንሣኤ
«ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና÷«ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው፤ ማቴ.፳፥፲፱፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ተሰውሮ ከሰነበተ በኋላ በዕለተ እሑድ በዝግ ቤት እንዳሉ ዳግም ተገለጸላቸው፤ስለዚህም ዳግም ትንሣኤ ተባለ፡፡
(ምንጭ:-መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ፤ ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ፤ ምዕ. ፳፥፳፬)