በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል አዘጋጅነት የባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር ጉባኤ ተደረገ

የኢ/ኦ/ተ ቤ/ክርስቲያንን አገልግሎት ለሕፃናት ፣ አዳጊዎችና ወጣቶች እንዲሁም ለተጠመቁና ለሚጠመቁ የውጭ አገር ዜጎች ለማድረስና ለማስፋፋት ከሚያገለግሉ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር ጉባኤ ተደረገ።

 

በሁሉም የባለድርሻ አካላት በተናጠል የሚሠሩ ሥራዎችን ለማጠናከርና በይበልጥም በቅንጅት ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች በመለየትና አቅምንና ሀብትን በተጠና መልኩ በማቀናጀት የሚፈለገውን ለውጥ በማምጣት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በውጭ ሀገር የጀመረችውን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ማፋጠን ይቻል ዘንድ ይህን የመጀመርያ የምክክር መድረክ በአሜሪካ ማዕከል አስተባባሪነት በየካቲት 9 2011 ዓ ም በዲሲ ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መዘጋጀቱ ተገልጿል። 

 

በመርሃ ግብሩም የዲሲና አከባቢዋ ሃገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልአከ አርያም ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና፣ ከሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መልአከ ሰላም ቀሲስ ዳኛቸው ካሳሁን፣ እንዲሁም ሥራው እየተሳተፉ ያሉ የካህናት ተወካዮች፣ የማኅበረ በዓለወልድ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ወጣቶች ሕብረት (UOTY)፣ የወጣት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች (YOTC) እና  የሰሜን አሜሪካ ሰ/ት/ቤቶች ህብረት (NASSU) አመራር አካላት፣ የርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ተወካዮች እና በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል አመራር አካላት እና አባላት ተሳትፈውበታል።e

በጉባኤውም በቀሲስ ሰይፈሥላሴ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና ካህናት እንዲሁም የጉባኤው ተሳታፊዎች የአገልግሎት ማኅበራት የአገልግሎት ልምዳቸውን ለጉባኤው አካፍለዋል። በመቀጠልም ህጻናትን፣ አዳጊዎችንና ወጣቶችን እንዲሁም የውጭ አገር ዜጎችን ትምህርተ ሃይማኖት ለማስተማርና ለድኅነት ለማብቃት የሚደረገው አገልግሎት ካለው የምእመናን ቁጥር ብዛት፣ የባህል፣ የቋንቋ ልዩነትና ከባቢያዊ ተጽእኖ አንጻር በቂ እንዳልሆነና ብዙ በተጠናና በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንደሚገባ በተሳታፊዎች ተጠቅሷል።

በመቀጠልም በአሜሪካ ማዕከል አመራር አካላት በማኅበረ ቅዱሳን 4ኛው ዙር ስልታዊ ዕቅድ መሠረት ለቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ትብብርና አቅም ማቀናጀት ወሳኝና አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም የባለድርሻ አካላት በጥናታዊ ጽሑፉና በውይይቱ የተጠቀሱትን የአገልግሎት ኃላፊነት በመውሰድ በታቀደና በሚለካ መልኩ መሥራት እንደሚገባ በአጽንኦት ተገልጿል።

 በመጨረሻም የዲሲና አከባቢዋ ሃገረ ስብከት ዋና ጸሃፊ መልአከ አርያም ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና  በሃገረ ስብከቱ ባሉ መዋቅሮች ይህንን አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ ለመደገፍና ለማስቀጠል ዝግጁነት እንዳለና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ማበርከት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለዚሁ የምክክር ጉባኤ ዝግጅት መሳካት የድርሻቸውን ለተወጡ ለዲሲ ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደርና ምዕመናን፣ ለዲሲና ቨርጂኒያ ንዑሳን ማዕከላት አባላትና ዝግጅቱን በበጎ ፈቃድ በድምጽ ወምስል በመቅረጽ ሙያዊ ድጋፍ ላበረከተው አቶ ሲሳይ አሸናፊ በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል መንፈሳዊ ምስጋና አቅርቧል።