በማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል አስተባባሪነት በተያዘው በጀት ዓመት ከተለያዩ አጥቢያዎች ለተወከሉ 59 የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በተለያዩ 3 ቦታዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተተኪ መምህራን ሥልጠና ተሰጠ።

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ትምህርት፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮና ምክር አገልግሎት ዋና ክፍል በተያዘው ዓመት በዲሲ፣ በሲያትልና በዳላስ ከአራት ንዑሳን ማዕከላት፣ ሦስት አጥቢያዎችና ሦስት ሰ/ት/ቤቶች ጋር በመተባበር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርተ ወንጌልን ማስተማር የሚችሉ 59 ሰባኪያንን አሠለጠነ፡፡ 

በማዕከሉ የትምህርት፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮና ምክር አገልግሎት ዋና ክፍል በተዘጋጀው በዚህ ሥልጠና ከተለያዩ አጥቢያዎች የተወከሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሙሉ ለሙሉ ተሳትፈዋል፡፡

 

በዋና ክፍሉ ሪፖርት እንደተገለጸው የሥልጠናው ዓላማ ሠልጣኞቹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወንጌልን ሊያዳርሱ የሚችሉበትን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ለማገዝ ሲኾን ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ)፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቤተክርስቲያን ታሪክና የስብከት ዘዴ በሥልጠናው የተካተቱ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው፡፡ ሥልጠናዎቹ የተሰጡትም ከየካቲት 8 እስከ 10 2011 ዓ.ም በዲሲና አከባቢው ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኘው ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል፣ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 2 ፣ 2011 ዓ.ም በሲያትል ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንና ከጥቅምት 16 እስከ 18 2011 ዓ.ም ደግሞ በዳላስ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ሥልጠናውን በመስጠትም ቀሲስ ሰይፈ ሥላሴ ጎርደን ከካንሳስ ሲቲ፣ ቀሲስ ሱራፌል ወንድሙ ከሲያትል እንዲሁም ዲ/ን ዓለማየሁ ደስታ ከዳላስ ተሳትፈዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በነበራቸው ቆይታ ከሥልጠናው ያገኙትን እውቀትና ልምድ በመጠቀምና የበለጠ በማስፋት ለቤተክርስቲያናቸው ሐዋርያዊ ተልዕኮ መፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ በመናገር በቀሰሙት የቤተክርስቲያን ትምህርት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ልዩ ልዩ ተሳትፎ በማድረግ ለሥልጠናው መሳካት ድርሻቸውን ለተወጡ ለዳላስ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደርና ምዕመናን፣ ለሲያትል ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደርና ምዕመናን፣ ለዲሲ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴደራል ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደርና ምዕመናን እንዲሁም ለደብሩ ፈለገ አበው ሰ/ት/ቤት፣ ለዲሲ ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የፍቅር ኅብረት ሰ/ት/ቤት፣ ለሜሪላንድ ኆኅተ ምሥራቅ አምደ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት እንዲሁም ለዲሲና ቨርጂኒያ ንዑሳን ማዕከላት የማዕከሉ የትምህርት፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮና ምክር አገልግሎት ዋና ክፍል በማኅበረ ቅዱሳን ስም መንፈሳዊ ምስጋና አቅርቧል፡፡

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰጠው የተተኪ መምህራን ሥልጠና እንደሚቀጥልና ከዚህ በፊት ሥልጠናውን ለወሰዱ የማጠናከሪያ ስልጠና፣ ላልወሰዱ ደግሞ  ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ይህንኑ ሥልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የአሜሪካ ማዕከል የትምህርት፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮና ምክር አገልግሎት ዋና ክፍል አስታውቋል፡፡