ዘገብርኄር (የዐቢይ ጾም ሰድስተኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምዕመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሰይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ፡፡ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምዕመን ዘበውኁድ ወምእመን ዘበውኁድ ምዕመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡

ትርጉም፡ ጌታው መልካም ሲሠራ አግኝቶ በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚሾመው ቸርና ታማኝ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር በታናሹ የታመንህ ደግና ታማኝ አገልጋይ ሆይ በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡

መዝሙሩንና ምንባባቱ በዜማ ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ

መልዕክታት

 ምንባብ 1 ( ፪ኛ ጢሞ. ፪ ቊ. ፩ – ፲፮)
እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል።የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ። በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ። ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤ ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና። ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤ ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው::

ምንባብ 2 (፩ኛ ጴጥ. ፭ ቊ. ፩ – ፲፪)
እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁምል ያበረታችሁማል። ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።

ምንባብ 3 (ሐዋ. ፩ ቊ. ፮ – ፱)
እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። እርሱም። አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።

ምስባክ ( መዝ. ፴፱ ቊ. ፰ – ፱)
ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ::
ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራሁ፡፡

ወንጌል ( ማቴ. ፳፭ ቊ. ፲፬ – ፴፩)

ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል።

ቅዳሴ: ዘባስልዮስ