ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ በሰሜን አሜሪካ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ
ቀሲስ ሳሙኤል ተስፋዬ መስከረም 23 ቀን 2011/October 3,2018
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ በሰሜን አሜሪካ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ ::
የግዕዝ ሥነ ጽሑፍና የብራና ቅርሶች በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካና የአውሮፓ ንዑሳን ማዕከላት አስተባባሪነት ከጥቅምት ፲-፲፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም/October 20-21/2018 በሰሜን አሜሪካ፣ አትላንታ ጆርጂያ በ 6202 Memorial Drive Stone Mountain, GA 30083 ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የዓለም አቀፍ ጥናት ጉባኤ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ (Ludwig Maximilian University, Munich, Germany) እና የኮሚቴ አባልና የዐውደ ጥናቱ አስተባባሪ ዶ/ር ፍሬሕይወት ወንድሙ (Wichita State University, USA) በጋራ እንደገለጹልን ለሁለተኛ ጊዜ በአሜሪካ አትላንታ ጆርጂያ ከተማ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የጥናት ጉባኤ፤ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ዐውደ ጥናት ጉባኤ በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል አስተባባሪነት በስዊድን ሉንድ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ከነበረው የዐውደ ጥናቱ ፋይዳ፣ ቀጣይነትና አቅጣጫዎች በመነሳት ሁለተኛው ዐውደ ጥናት በሰሜን አሜሪካ እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የዐውደ ጥናቱ ዋነኛ ዓላማም የኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስቲያንን በዓለም አቀፍ መድረክ ማስተዋወቅ ፣ በርካታ ምሥጢራትን ይዘው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶቻችን ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ፣ ጥናትና ምርምር የተደረገባቸውንም ቅርሶች በማወያየት ሀብቶቹ የሚጠበቁበትንና ለተሻለ አገልግሎት የሚበቁበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሆነ ገልጸውናል፡፡
የጥናቶቹን ይዘትና ማቅረቢያ ቋንቋ በተመለከተ ለኮሚቴው ተወካዮች ላቀረብነው ጥያቄ፤ ጥናቶቹ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሚቀርቡ ሲሆኑ በጉባኤው ላይ የሚቀርቡ ጥናታዊ ጽሑፎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱ ሆነው፤ የአንድምታ ትርጓሜ፣ገድላት፣ድርሳናት፣መልክአ መልኮች፣ቅኔ ፣ዜማ ፣የብራና ጽሑፎች ፣የመድኃኒት ይዘት ያላቸው ጥቅልል ጽሑፎች፣በብራና ውስጥ የሚገኙ ሥዕሎችና በዚህ ዝርዝር ላይ ያልተካተቱ ሌሎች ከጉባኤው ዓላማ ጋር የሚሄዱ ርእሶችም እንደሚቅቡ ገልጸውልናል፡፡
”ጥናት አቅራቢዎቹ በቤተክርስቲያናችን ቅርሶች ዙሪያ ጥናታዊ ምርምር የሚያካሂዱ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ሲሆኑ የጥናት አጠቃሎአቸውን ኮሚቴው ባስቀመጠው የመገምገሚያ መስፈርት መሰረት ነጥብ በመስጠት የተሻለ ነጥብ ያመጡት 13 ጥናቶች ለጉባኤው ሊቀርቡ ዝግጁዎች ናቸው፡፡ የተመረጡት የጽሑፍ አጠቃሎዎች በመጽሔት መልክ ታትመው በጉባኤው የሚሠራጩና በጉባኤው ላይ ቀርበው ውይይት የተደረገባቸውና መመዘኛውን የሚያሟሉ የጥናት ወረቀቶች ደግሞ በ“የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት” (Journal of Ethiopian Church Studies) እንዲታተሙ ይላካሉ፡፡” ሲሉም አስተባባሪዎቹ ገልጸውልናል፡፡
የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት13 ሲሆኑ በአውሮፓ፣በአሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ የማኀበረ ቅዱሳን አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማርና ጥናትና ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንናቸው፡፡ በተጨማሪም የውጭ ሃገር ዜጎች የሆኑ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ዜማና ብራና መጻሕፍት ላይ ምርምር እያደረጉ የሚገኙ ምሁራን በማማከር ስራዎች እየረዱ እነደሆነም ለመረዳት ችለናል፡፡
በዐውደ ጥናቱ ሦስት ቁልፍ ተናጋሪዎች (Keynote Speakers) ሲኖሩ እነዚህም፡-
1.ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ – የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ ሰሜን አሜሪካ፡፡
2.ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ – ሒል ሙዚየም (HMML)፣ ኮሌጅቪል፤ ሰሜን አሜሪካ፡፡
3.ፕሮፌሰር ስቲቭ ዴላማርተር – ጆርጅ ፎክስ ዩኒቨርሲቲ፣ ሰሜን አሜሪካ መሆናቸው ተገልጿል፡፡