በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል 21ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

ከዓርብ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ/ም እስከ ግንቦት 19 2011 ዓ/ም በኔቫዳ ግዛት ላስቬጋስ ከተማ “በሰላም ማሠሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” ኤፌ 4፡3 በሚል ኃይለ ቃል ሲካሄድ የሰነበተው በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል 21ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሰላም ተጠናቀቀ፡፡” .. ”

በአሜሪካ ማእከል ሥር ካሉት 12 ንኡሳን ማእከላትና 10 ግንኙነት ጣቢያዎች የመጡ የማኅበሩ አባላትና የአባላት ቤተሰቦች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ በላስ ቬጋስ ከተማ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የደብር አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ዲያቆናት ባጠቃላይ 372 ጉባኤተኞች የተሳተፉበት ይህ ጉባኤ ዓርብ ግንቦት 16 ቀን በሐመረ ኖህ ቅድስት ኪዳነምሕረት ወቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በጸሎት ተጀምሯል፡፡

በማግስቱ ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ/ም መርሐግብሩ በጸሎተ ወንጌል ከተከፈተ በኋላ በላስቬጋስ ንኡስ ማእከል ሕጻናት እና የአሜሪካ ማእከል መዘምራን የኅብረት መዝሙር አቅርበው መምህር ሙሉጌታ ኃይለማርያም የጠቅላላ ጉባኤውን መሪ ቃል “በሰላም ማሠሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” መነሻ አድርገው ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ ቀጥሎም በተከታታይ የአሜሪካ ማእከል መልእክት በማእከሉ ሰብሳቢ፣ የ2010/2011እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከማኅበሩ ስልታዊ እቅድ አንጻር በእቅድ ዝግጅት ክትትልና ጥናት ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የሂሳብ ክፍል ሪፖርት በሂሳብና ገቢ አሰባሳቢ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ እንዲሁም የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ሪፖርት በአገልግሎቱ ምክትል ኃላፊ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

ቅዳሜ ጠዋት መርሐግብር ፍጻሜ ላይ በሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ፈቃድ በማኅበረ ቅዱሳን 21ኛው ጠቅላላ ጉባኤ የሰሜን ካሊፎኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ተወካይ መጋቤ ምሥጢር አባ ቴዎድሮስ ዘውዱ ባስተላለፉት መልእክት በኅብረትና በአንድነት ማገልገል ያለውን ጠቀሜታ፡ አበክረው አስረድተዋል። በተጨማሪም ፡ ለሀገርም ፡ ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ መሥራት የሚቻለው መስመር ባለው ተቋማዊ አሠራር ይዞ በመሥራት ስለሆነ የማኅበሩ አባላት የተቋሙን አገልግሎት መጠበቅ እንደሚገባቸው ፤ በአገልግሎት ወቅት በሚመጡ የተለያዩ ፈተናዎች ተስፋ ሳይቆርጡ በአገልግሎት ጸንተው መንፈሳዊ ሕይወታቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ጉባኤው በቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በተያዘለት መርሐግብር መሠረት በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ሰፋ ያለ ተጨማሪ ውይይት ያደረገ ሲሆን “ወቅታዊ ሀገራዊ ለውጡን ከአገልግሎት አንጻር መረዳት” እና “የአኅጉረ ስብከት አገልግሎትን ለማጠናከር ያሉ በጎ እድሎችና ተግዳሮቶች” በሚሉ ሁለት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።

ቀጥሎም በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ የተተኪ ትውልድ ክፍል አስተባባሪነት በየኔታ ወልደገብርኤል ይታይህ የተዘጋጀው “በግእዝ ንባብ የውዳሴ ማርያም ጸሎት መማሪያ” ሲዲ ተመርቆ ለአገልግሎት እንዲተዋወቅ ተደርጓል፡፡ በዚሁም ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የተዘጋጀው የሕጻናትና አዳጊዎች ማስተማሪያ ሥርዓተ ትምህርት የመምህሩ መምሪያ አምስት መጻሕፍት በአሜሪካ ማእከል የተተኪ ትውልድ ክፍል በኩል ታትመው በአሜሪካ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ በነጻ ለሥርጭት መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
ከዚሁ መርሐግብር ተከትሎ በዝክረ አበው ወዕም መርሀ ግብር “የሰሙነ ሕማማት እንግዳ” በሚል ርዕስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለ32 ዓመታት በከፍተኛ ተጋድሎና ትጋት ስላገለገሉት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ/ ኃይለመስቀል/ የሚዘክር፡ አርያነታቸውንም የሚያስተምር ዝግጅት በበኩረ ትጉሃን ቀሲስ ኤርምያስ ቀርቧል፡፡

በእለቱ መርሐግብር ላይ የቤተ ማኅበረ ቅዱሳን ኮሚቴ ሰብሳቢ ስለ ቤተ ማኅበረ ቅዱሳን የኮሚቴውን የሥራ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በሪፖርታቸውም የአሜሪካ ማእከል የራሱ የሆነ የጽሕፈት ቤትና የሥራ ማስኬጃ ቦታ እንዲኖረው ለማድረግ የተደረገው ከፍተኛ ጥረትና ድካም ፍሬ ማፍራቱንና የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው ጉባኤተኛውም የግዥ ሂደቱን ለማቀላጠፍና ከብድር እዳ ነጻ የሆነ ሕንጻ ለመግዛት የሚያስፈልገውን ቀሪ ገንዘብ ለማዋጣትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡
በመጨረሻም በአባቶች ጸሎት የቅዳሜው መርሐግብር ተጠናቋል፡፡

እሑድ ጠዋት ለጉባኤው የመጡ ካህናት አባቶች እና አባላት በ ቬጋስ በሚገኙ የኢ/ኦ/ተ አብያተክርስቲያናት በተመደቡበት አጥቢያ በመገኘት ቀድሰዋል፣ አስቀድሰዋል። እሑድ ከሰዓት በኋላ በቀጠለው መርሐግብር የ2011/2012 ዓ.ም ዓመታዊ እቅድ የትኩረት አቅጣጫዎችና በጀት ለጉባኤው የቀረበ ሲሆን ጉባኤው በሶስት ምድብ በመሆን በእቅዶቹ ላይ ውይይት ተካሂዶባቸውል፡፡ እንዲሁም ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በእለቱ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ በአሜሪካ” እንደዚሁም “ለውጥ የሚያመጣ አገልግሎት” የሚሉ ዝግጅቶች ቀርበዋል። ለጉባኤው ከተጋበዙት ባለድርሻ አካላትም የበዓለወልድ ማኅበር፣ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት (NASSU)፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ወጣቶች ህብረት(UOTY)፣ እና የወጣት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች (YOTC ) መልእክት በተወካዮቻቸው ለጉባኤው ተነቧል።በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ካህናት አባቶች ተጋባዥ ወንድሞችና እህቶች በመንፈሳዊ ሕይወታችን ጠንክረን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ልናገልገል እንደሚገባ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

በመጨረሻም የ21ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት ኮሚቴ የሥራ ሪፖርትና ክንውን ሂደት ቀርቦ ከአባቶች ምስጋናና ጸሎት ተደርጎላቸዋል፡፡ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን የሕጻናትና አዳጊዎች መርሐግብር በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ 95 ልጆች እንደተሳተፉበትና በሦስት ደረጃ ተከፋፍለው እድሜያቸውን የሚመጥን ትምህርትና ዝግጅት እንደተከታተሉ ተገልጿል፡፡ ይህ የሕጻናትና አዳጊዎች መርሐግብር ትኩረት ተሰጥቶት ራሳቸው ልጆቹ ባለቤት ሆነው የሚያዘጋጁበት መንገድ በቀጣይም እንዲቀጥል ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ የአሜሪካ ማእከል የሚቀጥለው 22ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄደው በዴንቨር ኮሎራዶ መሆኑ በዚሁ ወቅት የተገለጸ ሲሆን መርሐግብሩ በዝማሬና በአባቶች ጸሎት እሑድ ሌሊት ተፈጽሟል፡፡