በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ 2ተኛውን ሐዊረ ሕይወት በተሳካ ሁኔታ አካሄደ

በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል  የኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ 2ተኛውን ሐዊረ ሕይወት በተሳካ ሁኔታ አካሄደ::

ግንኙነት ጣቢያው መነሻውን ከኢንዲያና ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በማድረግ ኦሃዮ ኮሎምበስ ወደሚገኘው የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቅዳሜ ፣ ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ. ም በኢንዲያና ዙሪያ የሚገኙ ከ70 በላይ ምዕመናንን ያሳተፈ መንፈሳዊ ጉዞ አካሂዷል።

የጉዞው ተሳታፊዎች በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቅጽር መገኘት የጀመሩት ከጠዋቱ 6:00 AM ሰዓት ቀደም ብለው ሲሆን ሁሉም ተሳታፊዎች በየተመደቡበት አውቶብስ ወይም ቫን መሳፈራቸው እንደተረጋገጠ በኢንዲያና ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ቀሲስ ንጉሤ ጸሎት ከተደረገ በኋላ ጉዞው ተጀምሯል። 3 ሰዓታት በፈጀው ጉዞ ተጓዦቹን በሐዋርያትና በቅዱሳን ስም በቡድን በመመደብ የመንፈሳዊ ጥያቄና መልስ ውድድር እንዲያደርጉ የተደረገ ሲሆን በጉዞው መጀመሪያና መጨረሻ በጋራ በመዘመር ጉዞው ልዩ መንፈሳዊ ድባብ እንዲኖረው ሆኗል።

ተጉዋዦቹ ኦሃዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ በደብሩ ካህናትና ምዕመናን አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ መርሐ ግብሩ በካናቱ መሪነት በጸሎት ተከፍቷል። በመቀጠልም የቁርስ መስተንግዶ በደብሩ ምዕመናን ተደርጎ ለእለቱ የተዘጋጁት መርሐ ግብራት  ቀጥለዋል። በእለቱ መልአከ አርያም ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና መስማትንስ ስላንተ ቀድሞ በጆሮዬ ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ በሚል ኃይለ ቃል መነሻነት እንዲሁም የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን ንሥሐ  በሚል ርዕስ ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን ጸሐፌ ትዕዛዝ መምህር ታዴዎስ ግርማ ደግሞ ሰፊ የዝማሬ አገልግሎት ሰጥተዋል ። እንዲሁም ከምዕመናን ለተነሱ ጥያቄዎች በመምህራኑ ምላሽ ተሰጥቷል።

በእለቱ የኢንዲያና ደብረ ሰላም  ቅዱስ ሚካኤል እና ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ትምህርት ቤቶች በጋራ መዝሙራትን ያቀረቡ ሲሆን ሦስት ታዳጊ ልጆች ደግሞ አባታችን በሰማያት ላይ ያለህ የሚለውን የበገና መዝሙር በጋራ አቅርበዋል።

በጉባኤው ከቀረቡት መርሐ ግብራት  የተሳታፊቹን ልዩ ትኩረት ያገኘው ዶ/ር በላይነህና ዲ/ን ፍሥሐ ያቀረቡት በማኅበረ  ቅዱሳን  ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ የሐዋርያዊ  አገልግሎት ማስፋፊያ ዋና ክፍል የተዘጋጀውን የአዳ አማንያን ጥምቀት ሪፖርት ፈተናዎችና  ቀጣይ ሥራዎች  የተመለከተ በቪዲዮ የታገዘ ገለጻ ሲሆን በተሳታፊዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ቁጭትን አሳድሯል። እንዲሁም የተወሰኑ ምዕመናንም ይህን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ቃል እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።

በኢንዲያናና አካባቢው የሚገኙ ምዕመናን ሰፊ ትምህርተ ወንጌል እንዲያገኙ ፣ ከተዘጋጀው የምክረ አበው እና ሰፊ የዝማሬ አገልግሎት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲበረቱ እንዲሁም ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲያገኙ ታስቦ በተዘጋጀው በዚህ ሐዊረ ሕይወት የተሳተፉት ምዕመናን በመንፈሳዊ ጉዞው መደሰታቸውን ገልጸዋል። እንዲሁም ለኦሃዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን $1,156.00 ዶላር መብዐ ሰብስበው ሰጥተዋል።

ለሐዊረ ሕይወቱ መሳካት የኢንዲያና ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን በመቀስቀስ ፣ የትራንስፖርትና የመሳሰሉትን ለጉዞ አስፈላጊ ነገሮች በማፈላለግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን የኦሃዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ ከአስተዳዳሪው ጀምሮ ሰበካ ጉባኤውና ምዕመናንኑ ለተጓዦቹ የቁርስና ምሳ መስተንዶ በማድረግ ፣ በደብሩ የተጋጀውን የ2011ዓ.ም ቀን መቁጠሪያ በነጻ በማደል እንዲሁም መርሐ ግብሩ የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በመጨረሻም ተጉዋዦቹን መርተው የሄዱት የኢንዲያና ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ቀሲስ ንጉሤ ገብሬ ለሐዊረ ሕይወት አስተባባሪዎቹ የማኅበረ ቅዱሳን ኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ ፣ ለአስተናጋጁ ደብር ኦሃዮ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፣ ለሁለቱ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በጉባኤው ላይ ለተገኙት ካህናት መዘምራን እና ምዕመናን ምስጋና አቅርበዋል። የማኅበረ ቅዱሳን ኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ ሰብሳቢ ዶ/ር ዓለማየሁ በበኩላቸው ለጉዞው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉት ካህናት ፣ አድባራት ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ተሳታፊ ምዕመናን ምስጋና አቅርበው መርሐ ግብሩ 5፡30 PM ላይ በጸሎት ተደምድሟል። ተጉዋዦቹም እየዘመሩ ወደ ኢንዲያና በሰላም ተመልሰዋል።