ግጻዌ ዘዕለተ ሰንበት

ጰራቅሊጦስ

መዝሙሩንና ምንባባቱን በዜማ ለማዳመጥ ከታች ያለውን audio ይጫኑ።

ሙሉ ምንባባቱን በPDF ለማግኘት እዚህ ይጫኑ።

እምዕርገት እስከ ጰራቅሊጦስ

መዝሙር:- በሰንበት ዐርገ ሐመረ (፯ተኛ እሑድ፥ እምድኅረ እርገት)

በሰንበት ዐርገ ሐመረ ገሠፀ ባሕረ። ወገሠፆሙ ለነፋሳት ወይቤሎሙ ኢትናፍቁ ወኢይምጻእ ኑፋቄ ውስተ ልብክሙ በከመ ፈነወኒ አቡየ አነኒ እፌንወክሙ። ውስተ ቤተ አቡየ ብዙኅ ማኅደር ቦቱ። ካዕበ እመጽእ ወእነሥአክሙ።ከመ ተሃልዉ ምስሌየ በመንግሥተ አቡየ ዘበሰማያት።

ትርጉም:- በሰንበት ከመርከብ ወጣ፥ ባሕርን ፀጥ አደረገ። ነፋሳትን ፀጥ አደረገ። አትጠራጠሩ፥ ጥርጥር ከልባችሁ አይግባ፥ አባቴ እንደላከኝ እኔም እልካችኋለሁ። ከአባቴ ቤት ብዙ ማደርያ አለ። ሁለተኛ እመጣለሁ፥ እወስዳችኋለሁ። ከእኔ ጋር እንድትኖሩ በሰማያት ባለ በአባቴ መንግሥት።

መልዕክታት

ምንባብ 1 (ሮሜ ፲ ቊ. ፩ – ፍ.ም.)

“ወንድሞች ሆይ፥ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው። በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።

ሙሴ ከሕግ የሆነውን ጽድቅ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት እንዲኖር ጽፎአልና። ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፦ በልብህ፦ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም፦ በልብህ፦ ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። መጽሐፍ፦ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና። በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።

እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።

ዳሩ ግን፦ ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት፦ ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። ነገር ግን፦ እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ፦ እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ ብሎአል። ኢሳይያስም ደፍሮ፦ ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ አለ። ስለ እስራኤል ግን፦ ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።”

ምንባብ 2 (፩ኛ ጴጥ. ፫ ቊ. ፲፭ – ፍ.ም.)

“በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና። ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤ እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።”

ምንባብ 3 (ሐዋ. ፩ ቊ. ፩ – ፲፪)

“ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤ ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን፦ ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ።

እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።

በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።”

ምስባክ (መዝ. ፵፮ ቊ. ፭ – ፯)

ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ። ወእግዚእነ በቃለ ቀርን። ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ።

ትርጉም:- አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ። ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፤

ወንጌል (ሉቃ. ፳፬ ቊ. ፵፭ – ፍ.ም.)

በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።

እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።”

ቅዳሴ:- ዘዲዮስቆሮስ

መዝሙሩንና ምንባባቱን በዜማ ለማዳመጥ ከታች ያለውን audio ይጫኑ።

ሙሉ ምንባባቱን በPDF ለማግኘት እዚህ ይጫኑ።