በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል 22ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል 22ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ።
ከግንቦት 14 እስከ 16, 2012 ዓ/ም “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን” 1ኛ ቆሮ 16፡14 በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የሰነበተው በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል 22ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሰላም ተጠናቀቀ፡፡ ጠቅላላ ጉባኤዉ በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ምክንያት በርቀት ከመደረጉ በቀር በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሟል። በጉባኤው ላይ ከ650 በላይ አባላት በርቀት በ’Zoom’ የተሳተፉ ሲሆን ጉባኤዉ በጊዜ አጠቃቀምም ሆነ በጉባኤው አባላት ሱታፌ ገጽ ለገጽ ከሚደረገው የጎደለ ሳይኖር የተፈጸመ ነበር።
የጉባኤው መክፈቻ ዓርብ ማታ በጸሎት የተጀመረ ሲሆን ዋናው ጉባኤ ቅዳሜ ጠዋት በሰሜን አሜሪካ ባሉ 3 ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኮሎራዶና አካባቢው ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳና አሪዞና ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የዋሽንግተን፣ ኦሪገን፣ አይዳሆና አካባቢው ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጸሎተ ወንጌል ተከፍቷል። በእለቱ መልአከ አርያም ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና የጠቅላላ ጉባኤውን መሪ ቃል “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን” መነሻ በማድረግ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ ቀጥሎም የአሜሪካ ማዕከል መልዕክት በማዕከሉ ሰብሳቢ በዲ/ን ተገኔ ተክሉ ቀርቦ በእለቱ የተገኙት ብፁዓን አባቶች መመሪያና ቃለ ምእዳን ሰጥተዋል። በመቀጠል 2011/2012 ዓ/ም እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከማኅበሩ ስልታዊ እቅድ አንጻር በእቅድ ዝግጅት ክትትልና ጥናት ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የሂሳብ ክፍል ሪፖርት በሂሳብና ገቢ አሰባሳቢ ዋና ክፍል ኃላፊ እንዲሁም የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ሪፖርት በአገልግሎቱ ኃላፊ ቀርቧል፡፡

በዚሁ እለት በዋናው ማዕከል ተወካይና የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ አቶ ታምሩ ለጋ የዋናው ማዕከል መልእክት የቀረበ ሲሆን ተሳታፊ አባላት በሪፖርቶቹ ላይ ያላቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች በጽሑፍ ከተሰበስቡ በኋላ በማእከሉ ስራ አስፈጻሚ አባላት ምላሽ ተሰጥቷል። ከቀረቡት አስተያየቶች ውስጥ ስምምነት የተደረሰባቸው በእቅድ ውስጥ እንዲካተቱ አቅጣጫ በመስጠት ጠቅላላ ጉባኤው የቀረቡትን እቅዶች አጽድቋል::

የእሁድ መርሐግብር በአባቶች ጸሎት ከተከፈተ በኋላ ቅዳሜ ዕለት በነበረው ጉባኤ በሪፖርቶቹ ላይ ከዋናው ማዕከል ተወካይ ግብረ መልስና አስተያየቶች የተሰጠ ሲሆን ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ሁኔታና የማኅበሩን አገልግሎት በተመለከተ በዋናው ማዕከል ተወካይ አጭር ገለጻ ተደርጓል። ከዚያም ማዕከሉን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚመሩ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን በማኅበሩ ደንብና አሠራር መሰረት በዕጣ እንዲመረጡ ተደርጓል:: በእለቱ የ2013 ዓ.ም እቅድ በዝርዝር ቀርቦ የጉባኤው ተሳታፊዎች በምድብ ተከፋፍለው ጥልቅ ውይይት ካደረጉበት በኋላ ሁሉም ቡድኖች ያነሷቸው በእቅድ ሊካተቱ የሚገባቸው ሃሳቦች እና በቀረበው እቅድ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ተካተው እቅዱ ጸድቋል:: ከአባቶችና ከጉባኤው ተሳታፊዎች አስተያየቶች ከተሰጡ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት በማዕከሉ ሥራ አስፈጻሚነት ላገለገሉና አዲስ ለተመረጡ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጸሎት ተደርጎል:: በመጨረሻም የ22ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት ኮሚቴ አጭር የሥራ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን የአሜሪካ ማእከል የሚቀጥለው 23ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በዚህ ዓመት ሊካሄድ ታስቦ በነበረበት በዴንቨር ኮሎራዶ እንደሚካሄድ ተገልጿል። በሁለቱም ቀናት በጉባኤው የተጋበዙ ማኅበራት ማኅበረ ባለወልድ፣ የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ UOTY፣ YOTC እና በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓና የካናዳ ማዕከላት ተወካዮች መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የአሜሪካ ማዕከል ከማኅበራቱ ጋር በመመካከር እየሰራቸው ያሉ ሥራዎችን የበለጠ በማጠናከር ለአንዲት ቤተክርስቲያን አገልግሎት መጠናከር በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። ጉባኤው በጸሎት ከተዘጋ በኋላ አባላቱ ሲዘምሩ ያመሹ ሲሆን ከ200 በላይ አባላትም ሌሊቱን ሙሉ ሲወያዮ አድረው ለ24 ሰዓት ጉባኤ ላይ መቆየታቸውን ሲገነዘቡ “ትናንት ያየናትን ፀሐይ እነሆ ደግመን አየናት” ሲሉ ኃይልና ብርታት የሰጣቸውን አምላክ አመስግነዋል::

ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን የአዳጊዎችና ወጣቶች 2ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ከ200 በላይ የአባላት ልጆችና የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በመርሐ ግብሩም ላይ ትምህርት፣ መዝሙር፣ ሥነ ጽሁፍ፣ የፓናል ዉይይትና ጥያቄና መልስ ቅዳሜና እሁድ በእያንዳንዱ ቀን ለ2 ሰዓታት ቀርቧል። ይህ የአዳጊዎችና ወጣቶች መርሐግብር ትኩረት ተሰጥቶት ራሳቸው ልጆቹ ባለቤት ሆነው የሚያዘጋጁበት መንገድ በቀጣይም እንዲቀጥል ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
የከርሞ ሰው ይበለን::

ማኅበረ ቅዱሳን በአትላንታ አስረኛውን የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ከፈተ!

 ቀን ነሐሴ 14 ቀን 2011

ማኅበረ ቅዱሳን  በአትላንታ አስረኛውን የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ከፈተ!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን  በሰሜን አሜሪካ ማዕከል የአትላንታ ንዑስ ማዕከል አስረኛውን የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ከፈተ፡፡

 

ከማዕከሉ የተተኪ ትውልድና ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ክፍል ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው ፤ ማዕከሉ ከ፸፭ (ሰባ አምስት) በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ  ለማስተማር  ዝግጅቱን አጠናቆ ሐምሌ ፳፯ ቀን ፳፻፲፩  ዓ.ም ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት  አገልግሎቱን መስጠት መጀመሩ ታውቋል።

 

ማኅበሩ በሰሜን አሜሪካ በሰባት የአሜሪካ ግዛቶች ማለትም በሲያትል ሦስት፣ በቨርጅኒያ፣ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በዳላስ፣ በቦስተን፣ በኖርዝ ካሮላይናና  በኢንዲያና የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከላትን ከፍቶ ከ ፭፻፶ (አምስት መቶ ሐምሳ) በላይ የሆኑ ልጆችንና አዳጊ ወጣቶችን ትምህርተ ሃይማኖት፣ አማርኛ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ የአብነት ትምህርትና የመሳሰሉ ትምህርቶችን ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ፤ አገልግሎቱን በማስፋት የአትላንታው የትምህርት ማዕከል መከፈት ማኅበሩ በሰሜን አሜሪካ  ያሉትን የትምህርት ማዕከላቱን  ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አስር ከፍ ያደርገዋል።

 

በተያያዘ ዜና የአትላንታ ንዑስ ማዕከል የተተኪ ትዉልድና ግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ክፍል ስምንት  የ፲፪ኛ (አስራ ሁለተኛ) ክፍል ተማሪዎችን በቅድመ ግቢ ጉባኤ መርኃ ግብር ለአራት ወራት  ኮርስ ሰጥቷል፡፡ ኮርሶቹም ፭ቱ አዕማደ ምስጢራት፣ ፯ቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገረ ክርስቶስ፣ ነገረ ማርያም፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክና  ነገረ ቅዱሳን ትምህርቶችን በመካነ ሕይወት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን በየሳምንቱ ቅዳሜ  ለሁለት ሰዓት ተኩል አስተምሮ ፤ ሰኔ ፱  ቀን ፳፻፲፩  ዓ.ም (June 15, 2019)  በአትላንታ ዳግማዊ ቁልቢ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ወተክለሃይማኖት በተክርስቲያን አስመርቋል።

 

 

በኢትዮ ሶማሌ ሀገረ ስብከት በተፈጸመው ኢ- ሰብአዊ ድርጊት ለተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት፣ ለተጐዱት ካህናትና ምእመናንን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው የድጋፍ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

በኢትዮ ሶማሌ ሀገረ ስብከት በተፈጸመው ኢ- ሰብአዊ ድርጊት ለተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት፣ ለተጐዱት ካህናትና ምእመናንን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው የድጋፍ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ፡፡

በተከሰተው ግርግርና ግጭት አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸው፤ ካህናትና ምእመናን መገደላቸው፤ ንዋየ ቅድሳት መዘረፋቸውና የአብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ምእመናን ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሰደዳቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን የተገለጸ ሲሆን እስካሁን የተደረገው ድጋፍ ከደረሰው ጉዳት አንጻር ዝቅተኛ በመሆኑ ድጋፉ ላይ ምእመናን ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡ Read more