ማኅበረ ቅዱሳን በአትላንታ አስረኛውን የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ከፈተ!

 ቀን ነሐሴ 14 ቀን 2011

ማኅበረ ቅዱሳን  በአትላንታ አስረኛውን የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ከፈተ!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን  በሰሜን አሜሪካ ማዕከል የአትላንታ ንዑስ ማዕከል አስረኛውን የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ከፈተ፡፡

 

ከማዕከሉ የተተኪ ትውልድና ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ክፍል ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው ፤ ማዕከሉ ከ፸፭ (ሰባ አምስት) በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ  ለማስተማር  ዝግጅቱን አጠናቆ ሐምሌ ፳፯ ቀን ፳፻፲፩  ዓ.ም ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት  አገልግሎቱን መስጠት መጀመሩ ታውቋል።

 

ማኅበሩ በሰሜን አሜሪካ በሰባት የአሜሪካ ግዛቶች ማለትም በሲያትል ሦስት፣ በቨርጅኒያ፣ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በዳላስ፣ በቦስተን፣ በኖርዝ ካሮላይናና  በኢንዲያና የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከላትን ከፍቶ ከ ፭፻፶ (አምስት መቶ ሐምሳ) በላይ የሆኑ ልጆችንና አዳጊ ወጣቶችን ትምህርተ ሃይማኖት፣ አማርኛ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ የአብነት ትምህርትና የመሳሰሉ ትምህርቶችን ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ፤ አገልግሎቱን በማስፋት የአትላንታው የትምህርት ማዕከል መከፈት ማኅበሩ በሰሜን አሜሪካ  ያሉትን የትምህርት ማዕከላቱን  ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አስር ከፍ ያደርገዋል።

 

በተያያዘ ዜና የአትላንታ ንዑስ ማዕከል የተተኪ ትዉልድና ግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ክፍል ስምንት  የ፲፪ኛ (አስራ ሁለተኛ) ክፍል ተማሪዎችን በቅድመ ግቢ ጉባኤ መርኃ ግብር ለአራት ወራት  ኮርስ ሰጥቷል፡፡ ኮርሶቹም ፭ቱ አዕማደ ምስጢራት፣ ፯ቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገረ ክርስቶስ፣ ነገረ ማርያም፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክና  ነገረ ቅዱሳን ትምህርቶችን በመካነ ሕይወት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን በየሳምንቱ ቅዳሜ  ለሁለት ሰዓት ተኩል አስተምሮ ፤ ሰኔ ፱  ቀን ፳፻፲፩  ዓ.ም (June 15, 2019)  በአትላንታ ዳግማዊ ቁልቢ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ወተክለሃይማኖት በተክርስቲያን አስመርቋል።