ሰሙነ ሕማማት (Passion week: Latin passio -suffering)

በኩረ ፍሥሐ ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ “ይደልዎነ ንአምን ከመ ቦቱ ለወልደ እግዚአብሔር ክልኤቱ ልደታት ቀዳማዊ ልደቱ እም እግዚአብሔር አብ እምቅድመ ኩሉ መዋዕል ወዳግማዊ ልደቱ እም እግእዝትነ ቅድስት ድንግል ማርያም በደኃራዊ መዋዕል” ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር ፮ ክፍል ፭
ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት አካል ዘእምአካል ባህሪ ዘእምባህሪ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል፤ ድህረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ የተወለደ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትሰብእቱ ፤ የሚባል ጌታ በተዋሕዶ ከበረ ብለን የቀናች የአባቶቻችን ሃይማኖታቸው ተዋሕዶን በማመን በመመስከር ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ስለ ሰሙነ ሕማማት እንማራለን ያነበብነውን ለበረከት ያድርግልን አሜን።

ሰሙን የሚለው ሰመነ- ስምንት አደረገ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲኾን ትርጕሙም ሳምንት፣ ስምንት ማለት ነው፡፡ ሕማማት የሚለዉ ሐመ -ታመመ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ብዙ ሕማምን ያመላክታል፡፡ ሰሙነ ሕማማት ስንልም የሕማም ሳምንት ማለታችን ነው፡፡

ለስም አጠራሩ የክብር ክብር ይግባውና የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት ፤ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ የሚያዜሙበት፤ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ የሚያነቡበትና የሚሰሙበት፤ በነግህ፣ በሠልስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት(ዘጠኝ ሰዓት) ፣ በሰርክ(በዐስራ አንድ ሰዓት) እየመላለሱ የሚሰግዱበትና የሚጸለዩበት ልዩ ሳምንት ነው

ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት:ከሰኞ እስከ ቅዳሜ

 

ዕለተ ሰኑይ (ሰኞ)
በዕለተ ሰኑይ አንጾሖተ ቤተ መቅደስ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ነው
ማቴ ፳፩፥፲፰፡፳፪ ፤ ማር ፲፩፥፲፪፡፲፬ ጌታችን ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ከሩቁ አይቶ በለሲቱን ቀረባት ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አልተገኘባትም ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንች ፍሬን አይብላ ብሎ እረገማት፡፡በለስ የተባሉ እስራኤላዊያን ናቸዉ አብርሃም አባት አለን ከማለት በቀር ምግባር ፍሬ አልተገኘባቸውምና፤ እንድም በአንጻረ በለስ ረገማ ለኃጢአት እንዲል እንደ በለስ ቅጠል በዚህ ዐለም ሰፍታ የነበረች ኃጢአትን ረገማት ፈጥናም ጠፍች
ማቴ ፳፩፥፲፫ ይህ ቀን አንጽሖተ ቤተመቅደስ የፈጸመበት ነው ።ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” በማለት ከቤተ መቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋል።

ዕለተ ሠሉስ (ማክሰኞ)
ማቴ ፳፩፥፳፫፡፳፯ ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን “በማን ሥልጣን ታደርጋለህ ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ” የሚል ነበር ጌታችንም “እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል” ሲል አስተምሯል፡፡
ዕለተ ረቡዕ
የአይሁድ ሊቃነ ካህናት እና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸዉ ምክር ያጠናቀቁበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል፡፡
ዕለተ ሐሙስ
በቤተ ክርስቲያን የተለያየ ስያሜዎች ያሏቸዉ በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ነዉ፡፡
ጸሎተ ሐሙስ ይባላል መድኃኒዓለም ክርስቶስ አይሁድ መጥተዉ እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ስለሆነ
ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር ጎንበስ ብሎ በታላቅ ትሕትና አጥቧልና
የምሥጢር ቀን ይባላል ከሰባቱ ምሥጢራት አንዱ የሆነዉ ምሥጢረ ቁርባን በዚህ ዕለት ተመስርቷልና ነዉ፡፡
የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል የኦሪት መስዋዕት የሆነዉ የእንስሳት ደም ማብቃቱን ገልጦ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ

አይሁድ ጌታችንን የያዙበት ቀን ስለ ኾነ በዚህ ዕለት በለኆሣሥ (ብዙ የድምፅ ጩኸት ሳይሰማ) የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ መላው ሕዝበ ክርስቲያን የሕጽበት፣ የምሥጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሐ ታጥበው፣ ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዓርብ

ዕለተ ዓርብ እኛ የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት (ቁራኝነት) እንኖርበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመባትና ፍጹም ድኅነት ያገኘንባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ዅልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ የክርስቶስን ሕማሙን፣ ስቅለቱንና ሞቱን የምናስብበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት፤ የሕይወት መቅጫ አርማ ኾኖ ሳለ ለእኛ ግን የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት ዕለቱ ‹መልካሙ ዓርብ› በመባል ይታወቃል፡፡

ዕለተ ቅዳሜ

በዚች ዕለት የጌታችን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትዉል ቀዳሚት ሥዑር ወይም የተሻረችዉ ቅዳሜ ትባላለች፡፡ካህናቱም ለምዕመናን ለምለም ቄጤማን የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ ለምለም ቅዳሜም ትባላለች፡፡

ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን

ዋቢ: አንድምታ ወንጌል፤ መጽሐፈ ግጻዌ እና ከዚህ በፊት በዐለ ሆሣዕናን አስመልክቶ በማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ ላይ የወጡ ጽሑፎች

ወስብሐት ለእግዚአብሔር