በአሜሪካ ማእከል የካሮላይና ግንኙነት ጣቢያ የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አስመረቀ
በማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል ካሮላይና ግንኙነት ጣቢያ የሚገኘው የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ለሁለት ወራት የክረምት ትምህርት ያስተማራቸውን ሰባ ስድስት (፸፮) ተማሪዎች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት በመስጠት የክረምቱን መርሃ ግብር ነሐሴ ፲፱ ቀን ፳፻፲ ዓም አጠናቋል። በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ በሻርለት ኖርዝ ካሮላይና የመካነ ብርሃን ቅድሥት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መሪጌታ ሰናይ ተገኝተው ሕጻናቱንና አዳጊ ወጣቶችን ባርከው አበረታትተዋቸዋል። በዚህ የክረምት ትምህርት መርሃ ግብር ላይ ተጋባዥ እንግዶችና የተመራቂ ሕጻናቱና አዳጊ ወጣቶቹ ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን በአጠቃላይ በክረምቱ መርሃ ግብር ላይ የወላጆች ሱታፌ የላቀ እንደነበር የትምህርትና ሥልጠና ማዕከሉ አስተባባሪዎች ገልጠዋል።
ማዕከሉ በሚቀጥለው ዙር የሚያስተምራቸውንም ተማሪዎች መመዝገቡን ከአስተባባሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።