ዘምኲራብ (የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፡፡

ትርጉም: ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡)፡ ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።

መልዕክታት

ምንባብ (ቆላ. 2÷16-ፍጻ.)፡

እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ÷ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር፡፡ ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት÷ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት÷ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት በሚሞላበትም በራስ አይጸናም፡፡

ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርሰቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ? እንዴትስ ይህን አትዳስስ÷ ይህን አትንካ÷ ይህንም አትቅመስ ይሉአችኋል? ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና፡፡ ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት÷ ለሥጋም ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም፡፡

ምንባብ (ያዕ. 2÷14-ፍጻ.)፡

ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ÷ “በሰላም ሂዱ÷ እሳት ሙቁ÷ ትጠግባላችሁም” ቢላቸው÷ ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡

ነገር ግን አንድ ሰው÷ “አንተ እምነት አለህ÷ እኔም መልካም ሥራ አለኝ፤ እስቲ ሃይማኖትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ” ይላል፡፡ አንተም እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ ታምናለህ፤ መልካምም ታደርጋለህ፤ እንዲህስ አጋንንትም ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም፡፡ አንተ ሰነፍ ሰው÷ እምነት ያለ ምግባር የሞተች እንደ ሆነች ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊያው ባቀረበው ጊዜ÷ በሥራው የጸደቀ አይደለምን? እምነት ለሥራ ትረዳው እንደ ነበር÷ በሥራውም እምነቱ እንደ መላችና ፍጽምት እንደ ሆነችም ታያለህን?

ምንባብ (የሐዋ.10÷1-8)

በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር፡፡ እርሱም ጻድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ÷ “ቆርኔሌዎስ ሆይ÷” አለው፡፡ ወደ እርሱም ተመልክቶ ፈራና÷ “አቤቱ÷ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው÷ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል፡፡ አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ፡፡ እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል፡፡ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡” ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት÷ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ፡፡

ምስባክ

መዝ.68፡9፡-

እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ ትዕይርቶሙ ለእለይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፤ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

ትርጉም፦ የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፡፡

ወንጌል (ዮሐ. 2÷12-ፍጻ.)፡-

ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ÷ ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ፡፡ የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን÷ ርግቦችንም የሚሸጡትን÷ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን÷ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡ ርግብ ሻጮችንም÷ “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም÷ “የቤትህ ቅናት በላኝ” የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ፡፡

አይሁድም መልሰው÷ “ይህን የምታደርግ ምን ምልክት ታሳያለህ?” አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም÷ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው፡፡ አይሁድም÷ “ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፤ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሣዋለህን?” አሉት፡፡ እርሱ ግን ይህን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለ ተባለ ሰውነቱ ነበር፡፡ ከሙታን በተነሣ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንደ ነገራቸው ዐሰቡ፤ በመጻሕፍት ቃልና ጌታችን ኢየሱስ በነገራቸውም ነገር አመኑ፡፡

ቅዳሴ: ዘእግዚእነ

መዝሙሩንና ምንባባቱ በዜማ ለማዳመጥ ይህን ይጫኑ