ዘሆሣዕና (የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት)

ሆሣዕና (የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ ለአምላከ ጽድቅ፡፡ ኅበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዓቀብ ሀገረ እግዚአብሔር፡፡ ወተቀበልዎ ሕዝብ በዙኃን አዕሩግ ወሕፃናት ነሢኦሙ አዕፁቀ በቀልት እንዘ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ተፅ ዒኖ ዲበ ዕዋል ቦአ ሀገረ ኢየሩሳሌም በትፍሥሕት ወበሤት ይሁቦሙ ኃይለ ወሥልጣነ፡፡

ትርጉም፡ የፋሲካ በዓል ሳምንት ሲቀረው የእውነተኛው አምላክ ደቀ መዛሙርት የእግዚአብሔር አገር ወደ ሆነችው ደብረ ዘይት ቁልቁለት ሲደርሱ ወደ እርሱ ለመታዘዝ ቀቡ፤ ብዙ ሕዝብ፣ ልጆችና ሽማግሌዎችም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ሆሣዕና በአርያም እያሉ ተቀበሉት፡፡ በአህያ ተጭኖ ኃይልና ሥልጣንን ይሰጣቸው ዘንድ በፍጹም ደስታ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡

መልዕክታት

የሆሣዕና ምንባብ 1 ( ዕብ. ፱ ቊ. ፲፩ – ፳፰ )

ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው። ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፤ ሰው ሲሞት ኑዛዜው ይጸናልና፥ ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን ከቶ አይጠቅምም። ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልተመረቀም። ሙሴም ትእዛዛትን ሁሉ እንደ ሕጉ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ፥ የጥጆችንና የፍየሎችን ደም ከውኃና ከቀይ የበግ ጠጕር ከሂሶጵም ጋር ይዞ። እግዚአብሔር ያዘዘላችሁ የኪዳን ደም ይህ ነው ብሎ በመጽሐፉና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ረጨው። እንዲሁም በድንኳኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ደምን ረጨ። እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም። እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።

የሆሣዕና ምንባብ 2 ( ፩ኛ. ፬ ቊ. ፩-፪ – ፲፪)

ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና። የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና። በዚህም ነገር ወደዚያ መዳራት ብዛት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እየተሳደቡ ይደነቃሉ፤ ግን እነርሱ በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። እንደሰዎች በሥጋ እንዲፈረድባቸው በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር እንዲኖሩ ስለዚህ ምክንያት ወንጌል ለሙታን ደግሞ ተሰብኮላቸው ነበርና። ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ፤ ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤

የሆሣዕና ምንባብ 3 (ሐዋ.  ፳፰ ቊ. ፲፩ – ፍም)   

ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፥ በእርሱም የዲዮስቆሮስ አላማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤ ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን። በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን። ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና። ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት። ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ። እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤ አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና። እነርሱም። እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፥ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም ወይም አልተናገረብህም። ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን አሉት። ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር። እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፥ እኵሌቶቹ ግን አላመኑም፤ እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ። መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን። ወደዚህ ሕዝብ ሂድና። መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤ በዓይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል። ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ። ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።

ምስባክ  ( መዝ. ፰ ቊ. ፪ – ፫)

እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳከ ስብሐተ። በእንተ ጸላኢ። ከመ ትንሥቶ ለጸላኢ ወለገፋዒ።

ትርጉም፦ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት።

 

የሆሣዕና ምንባብ ወንጌል ( ዮሐ. ፭ ቊ. ፲፩ – ፴፩)

እርሱ ግን። ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት። ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም።ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና። እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ። እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም፤ ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፥ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደ ሆነ አውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል። እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ።