ሆሣዕና(Palm Sunday)

በኩረ ፍሥሐ ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ “ይደልዎነ ንአምን ከመ ቦቱ ለወልደ እግዚአብሔር ክልኤቱ ልደታት ቀዳማዊ ልደቱ እም እግዚአብሔር አብ እምቅድመ ኩሉ መዋዕል ወዳግማዊ ልደቱ እም እግእዝትነ ቅድስት ድንግል ማርያም በደኃራዊ መዋዕል” ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር ፮ ክፍል ፭
ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት አካል ዘእምአካል ባህሪ ዘእምባህሪ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል፤ ድህረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ የተወለደ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትሰብእቱ ፤ የሚባል ጌታ በተዋሕዶ ከበረ ብለን የቀናች የአባቶቻችን ሃይማኖታቸው ተዋሕዶን በማመን በመመስከር ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ስለ ሆሣዕና  እንማራለን ያነበብነውን ለበረከት ያድርግልን አሜን።

ሆሣዕና  “הושענא ሆሻአና” የዕብራይስጥ ቃል ሲኾን  ትርጒሙም “አቤቱ አሁን አድን” ማለት ነው(Latin osanna, Greek ὡσαννά, hōsanná )። በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ከጌታችን መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ፱ኙ ዐበይት በዓላት ውስጥ አንዱ በዓለ ሆሣዕና ነው።

“ይጸውር ድደ ወይነብር ጠፈረ ኲሉ እኁዝ ውስተ እራኁ ወአጽናፈ ዓለም በእዴሁ” (በጠፈር ተቀምጦ መሠረትን ይሸከማል፤ ሁሉ በመኻል እጁ የተያዘ የዓለም ዳርቾችም በእጁ ያሉ)ተብሎ የሚነገርለት፤ ሰምይ ዙፍኑ ምድርም የእግሩ መረገጫ የሆነችለት፤  በኪሩቤልና በሱራፌል በጸጋ አድሮ የሚገለጥ ጌታ፤ የተናቀውን የሚያከብር አምላክ ወሰብእ፤ በትሕትና በአህያና በውርንጫይቱ ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የነቢያት ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት ዕጓለ ርግብ ዘውገ ማዕነቅ ይዘው ጥበብ ከሠተት አፈ ሕፃናት እንዲል በንጹሕ አንደበታቸው  ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ዕለት ነው።

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ በደብረ ዘይት አጠገብ ከምትገኝ ቤተ ፋጌ ሲደርስ ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ በዚያም አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፤ ፈታችሁ አምጡልኝ ፤ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ ሲል ላካቸው። መንደር የሲዖል ፣ አህያይቱና ውርንጫይቱ የአዳምና የልጆቹ ፣ በመንደር መታሰራቸው አዳምና ልጆቹ በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ ተይዘው በሲዖል በባርነት መኖራቸውንና ጌታችንም የሲዖል ባርነት አስወግዶ ነጻነትን የሚያድልበት ጊዜ እንደቀረበ ያጠይቃል። ዛሬም እኛ ልጆቹ በማዕሰረ ኃጢአት ተይዘን ከእርሱ ስንርቅ ከማዕሰረ ኃጢአት ፈትተው ወደርሱ የሚያቀርቡንን ካህናትን ሰጥቶናል።

ደቀ መዛሙርቱም ሄደው አህያይቱንና ውርንጫይቱን አመጡለት ፤ ልብስ የአካልን ነውር እንደሚሰውር አንተም ከባቴ አበሳ ነህ ሲሉ ልብሳቸውን እንደኮርቻ ጎዘጎዙለት። አምላካችንም በሁለቱም ላይ በጥበብ ተቀመጠባቸው። በአህያ መቀመጡ ስለ ምን ነው  ቢሉ ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም።

ትንቢት “የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ዘካ ፱፥፱

ምሳሌ ቀድሞ አባቶች ነቢያት ዘመነ ጸብዕ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ፤ ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረሰ ሲል።

  • በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም ፤ እርሱም ካልፈልጉኝ አልገኝም ከሹኝም አልታጣም ሲል።
  • በትሑታን አድሬባቸው እኖራለው ሲል።
  • አህያ ቀንበር መሸከም የለመደች እንደሆነች እስራኤልም ሕግ መጠበቅ ለምደዋልና ውርንጫይቱ ቀንበር መሸከም ያልለመደች እንደሆነች አሕዛብም ሕግ መጠበቅ ያልለመዱ ናቸውና።
  • አህያ የኦሪት ምሳሌ ኦሪት የተለመደች ሕግ ናትና ፤ ውርንጫይቱ የወንጌል ምሳሌ ወንጌል ያልተለመደች ሕግ ናትና።

ከሕዝቡም ብዙዎች እንኳን ለአንተ የተቀመጥክበትም መሬት መንካት አይገባውም ሲሉ ልብሳቸውን በጎዳና አነጠፉለት። አንድም በአዩ ልማድ
ኤልሳዕ አዩን ቅብዐ መንግሥት በቀባው ጊዜ ከጓደኞቹ እኩሌቶቹ አነጽፈዋል እኩሌቶቹም ጋርደዋል።አብርሃም ይስሐቅን፣ይስሐቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ ፣ እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ ሰሌን ይዘው አመስግነዋልና በአበው ልማድ ሌሎቹም ከዛፍ (ዘንባባ ፣ ቴምርና ወይራ) ጫፍ ጫፉን እየቆረጡ ከመንገድ ያነጥፉ ነበር። ዘንባባ እሾሀማ ነው ትምህርተ መዊዕ አለህ ሲሉ ፣ ለብልቦ ይተወዋል እንጂ እሳት አይበላውም ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ። ቴምር ልዑል ነው ልዑለ ባህርይ ነህ ሲሉ ፤ ፍሬው አንድ ነው ዋህደ ባህርይ ነህ ሲሉ ፤ ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ ትንቢቱን አውቆ አናግሯል። ምሳሌውንም እንጂ አውቆ አስመስሏል።

የበዐለ ሆሣዕና ዑደት

በቤተ መቅደስ

ምስባክ መዝ ፻፲፯፥፳፮፡፳፯

ሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤
ባረክናክሙ እምቤተ እግዚአብሔር
እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ

ወንጌል ሉቃ ፲፱፥፩

አቡን አርእዩነ ፍኖቶ
ሃሌ  ሃሌ ሉያ ፣ አርእዩነ ፍኖቶ፣ ወንሑር ቤቶ፣ እስመ እምጽዮን ፣ይወጽእ ሕግ ፣ወቃለ እግዚአብሔር እምኢየሩሳሌም፣ ንሣለማ ለመድኃኒትነ፣ በትፍሥሕት፣ ተቀበልዋ ለታቦት፣ እስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን

ምልጣን ንሳለማ ለመድኃኒትነ በትፍሥሕት ተቀበልዋ ለታቦት እስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን
ምዕዋድ  እስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን ዋካ ይእቲ ወብርሃን

በምዕራብ

ምስባክ መዝ ፱፥፲፩ ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘየኀድር ውስተ ጽዮን፣ ወንግርዎሙ  ለአሕዛብ ምግባሮ ። እስመ ተዘከረ ዘይትኃሠሥ ደሞሙ

ወንጌል ዘማቴዎስ ማቴ ፳፩፥፩፡፲፯

አቡን ሰመያ አብርሃም

ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፣ ሃሌ ሃሌ ሉያ፣ ሃሌ ሃሌ  ሉያ፣ሰመያ አብርሃም፣ ወይቤላ፣ ዛቲ ዕለት በዓለ እግዚአብሔር፣ ንፍሑ ቀርነ ፣በዕለተ ሠርቅ፣ በዕምርት ዕለት፣ በዓልነ፣ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን

ምልጣን ንፍሑ ቀርነ ፣በዕለተ ሠርቅ፣ በዕምርት ዕለት፣ በዓልነ፣ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን

ምዕዋድ ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን

በደቡብ

ምስባክ መዝ.፰፥፪

“እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሓተ፡፡ በእንተ ጸላዒ፡፡ ከመ ትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ፡፡”

ወንጌል ማር ፲፩፥፩፡፲፩

አቡን ወትቤ ጽዮን

ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፣ ሃሌ ሃሌ ሉያ፣ ሃሌ ሃሌ  ሉያ፣ወትቤ ጽዮን፣ አርኅው ሊተ አናቅጸ ፣ይባኡ ሕዝብ ብዙኃን፣ ወያዕትቱ፣ ዕብነ እምፍኖት፣ ለንጉሥ  ለወልደ ዳዊት፣ ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ፣ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም

ምልጣን ወያዕትቱ፣ ዕብነ እምፍኖት፣ ለንጉሥ  ለወልደ ዳዊት፣ ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ፣ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም

ምዕዋድ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ይብሉ ሆሣዕና በአርያም

በምሥራቅ

ምስባክ መዝ ፵፱፥፩

እምሥራቀ ፀሐይ እስከነ ዓረብ ይትአኰት ስሙ ለእግዚአብሔር ልዑል እግዚአብሔር መልዕልተ ኵሉ አሕዛብ።

ወንጌል  ሉቃ ፲፱፥፳፰

አቡን  ባርኮ ያዕቆብ

ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ፣ሃሌ ሃሌ ሉያ ፣ሃሌ ሃሌ  ሉያ፣
ባረኮ ያዕቆብ፣ ለይሁዳ ወልዱ ወይቤሎ፣ሀሎ ንጉሥ ዘይወጽ እምኔከ ፣ዘየሐጽብ ፣በወይን ልብሶ፣ወበደመ ፣አስካል ሰንዱኖ ፣ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ ፣ይብሉ ሆሣዕና በአርያም

ምልጣን ዘየሐጽብ ፣በወይን ልብሶ፣ወበደመ ፣አስካል ሰንዱኖ ፣ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ፣ይብሉ ሆሣዕና በአርያም
ምዕዋድ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ይብሉ ሆሣዕና በአርያም

በሰሜን

ምስባክ መዝ.፹÷፫  ንፍሑ ቀርነ በዕለተ ሠርቅ በእምርት ዕለት በዓልነ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ

ወንጌል ዮሐ ፲፪፥፲፪፡፲፱

አቡን ባኡ ውስተ ሀገር
ሃሌ ሃሌ  ሉያ ባኡ ውስተ ሀገር  ወበዊአክሙ ትረክቡ ዕዋላ አድግ እሱረ ፍትህዎ ወአምጽእዎ ሊተ።

ምልጣን ፍትህዎ ወአምጽእዎ ሊተ።ፍትህዎ ወአምጽእዎ ሊተ።

ምዕዋድ ፍትህዎ ወአምጽእዎ ሊተ ፍትህዎ ወአምጽእዎ ሊተ።

ካህናት ወደቤተ መቅደስ ሲመለሱ

አቡን  ሃሌ ሉያ አልጺቆ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ርእያ ለሀገር፤ ወይቤላ ሶበ ተአምሪ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ በጽሐ ብርሃነኪ ዮም ሰላምኪ።

ምልጣን ወይቤላ ሶበ ተአምሪ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ በጽሐ ብርሃነኪ ዮም ሰላምኪ በሕዝብኪ ዮም ሰላምኪ  ይትሐፈሩ ጸላእትኪ ዮም ሰላምኪ፤ሰላምኪ ሰላምኪ ዮም ሰላምኪ

ሥርዓተ ቅዳሴ ዘሆሣዕና

በዕለተ ሆሣዕና  የቅዳሴው አገባብ ሥርዓት ከሌሎች ዕለታት ለየት ያለ ነው፡፡ ዲያቆናቱ ኅብስቱን በመሶበ ወርቅ ወይኑን በጽዋዕ ይዘው በምዕራብ በር በኩል ይቆማሉ፡፡ ሠራኢው ዲያቆን በዜማ አሰምቶ “አርኍ ኖኃተ መኳንንት፣ አለቆች ደጆችን በሮችን ክፈቱ” ይላል ካህኑም በመንጦላዕት ውስጥ ሆኖ “መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት መኑ ውእቱ ዝንቱ አምላከ ምሕረት-ይህ  የክብር ንጉሥ የኃያላን አምላክ ማነው”ይላል ሠራኢው ዲያቆንም መልሶ “እግዚአብሔር አምላከ ኃያላን ውእቱ ንጉሠ ስብሐት አርኍ ኖኃተ መኳንንት- ይህ  የክብር ንጉሥ የኃያላን አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ ብሎ ይመልሳል፡፡ ካህኑም  መንጦላዕቱን እየገለጠ “ይባእ ንጉሠ ስብሐት ይባእ አምላከ ምሕረት- የክብር ንጉሥ ይግባ” ብሎ ፈቅዶለት ይገባል መዝ ፳፫፥፯፡፡

ይህንንም አበው እንደሚከተለው ያመሰጥሩታል፤ አንደኛ ቅዱስ ገብርኤልና ወላዲተ አምላክ በምሥጢረ ብስራት ጊዜ የተነጋገሩት እንደሆነና በመጨረሻም “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ መቀበሏን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ፈያታዊ ዘየማንና መልአኩ ኪሩብ በማእከለ ገነት የተነጋገሩትን በድርጊት ለማሳየት መሆኑን ያስተምራሉ፡፡ ዋናው ምሥጢር ግን ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሊገባ ሲል ብዙዎቹ እንዳይገባ ቢፈልጉም ከፊሎቹ ግን እንዲገባ መፍቀዳቸውን ያሳያል፡፡እንደተለመደው ሥርዓተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ “እግዚአ ሕያዋን” የሕያዋን ጌታ የተሰኘው ጸሎት በካህናት ተደርሶ ለምእመናን ሥርዓተ ፍትሐት ይደረግላቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሥርዓተ ፍትሐት ስለማይደረግ፤ በሰሙነ ሕማማት የማይከናወኑ ምሥጢራት በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናል፡፡

ምእመናኑ ተባርኮ የተሰጣቸውን የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ወደ ቤታቸው ያመራሉ፡፡ የዘንባባው ምሥጢር የተጀመረው በታላቁ አባት በአብርሃም ነው ኩፋ ፲፫፥፳፩፡፡ ይህን የአባታቸውን ሥርዓት አብነት አድርገው እስራኤል የኤርትራን ባሕር ሲሻገሩ፣ ዮዲት ድል ባደረገች ወቅት ዘንባባ እየያዙ እግዚአብሔርን አመስግነውበታል፡፡ ጌታችን በዕለተ ሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም ሽማግሌዎችና ሕፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ሆሣዕና በአርያም ብለው አመስግነውታል ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር