የካህናት ኃላፊነትና የምእመናን ድርሻ

ጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲ ላይ “ኖላዊ ኄር ቸር እረኛ እኔ ነኝ” ሲል አስተምሯል። በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን ስለአመጣጡ – ትንቢት ተነገሮለት፣ ሱባዔ ተቆጥሮለት፣ የባህርይ አባቱ እግዚአብሔር አብ መስክሮለት የመጣ መሆኑን፣ የመጣውም ለምኅረትና ለቤዛነት መሆኑን ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለፍጥረቱ /ለበጎች/ ምእመን የሚራራ ቸር ጠባቂ መሆኑን አስተምሮበታል። ትምህርቱ ጥልቅ መንፈሳዊ መልእክት ያለውና በተለይም የካህናትን /የአገልጋዮችን/ ኃላፊነት በሚገባ የሚያስገዘብ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ኤጲስ ቆጶሳትና ቀሳውስት ሲሾሙ የሚተረጎም እንደሆነ ከቅዱስ ድሜጥሮስ ሹመት ጋር ተያይዞ በሚተረከው ታሪክ ላይ ተጠቅሶ ይገኛል።
ጌታችን የአዳም ልጆች ሁሉሞት ሰልጥኖባቸው፣ በዲያቢሎስ አገዛዝ ስር ሆነው፣ በገቢረ ኃጢኣት ተይዘው ሲቅበዘበዙ ሞትን ለመደምሰስ፣ ከዲያቢሎስ አገዛዝ ነጻ ለማውጣትና በጎች የተባሉ ምእመናንን በለመለመች መስክ በቤተ ክርስቲያን በማሰማራት የሕይወት ውሃ የተባለ ቃሉን ለመመገብ ነው። ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።” (፩ጴጥ ፪፡ ፳፬-፳፭) በማለት ገልጾታል።
መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ትንቢት የተነገረለት ቸር ጠባቂ መሆኑን አስቀድሞ በልዑለ ቃል ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተነግሯል። “ እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።” (ኢሳ ፵፣፲-፲፩) እውነትም እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጥረቱን በቸርነቱ የሚመግብ፣ የፈጠረውን ፍጥረት ድካም የሚረዳ፣ በኃጢአትና በቀቢጸ ተስፋ የወደቁትን በርኅራኄና በፍቅር የሚያሰማራ ቸር ጠባቂ ነው። ቸር ጠባቂነቱ የተረጋገጠውም ሕጉን ጥሶ፣ አምላክነትን ሽቶ፣ ከገነት ለተባረረው ለአዳምና ልጆቹ /ለበጎቹ/ ነፍሱን አሳልፎ በመስጠቱ ነው።
የካህናት ሹመት
ለቤዛ ዓለምና ለአርአያነት የመጣው ጌታ በዘመነ ሥጋዌው ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ በደሙ የዋጃቸውን ምእመናንን የሚጠብቁና የሚያሰማሩ ካህናትን መሾም ነው። ሐዋርያት በአንብሮተ እድ (እጅ በመጫን) ሲሾሙና የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ /ሥልጣን/ ሲሰጣቸው በተግባር ጌታችን ያስተማረውን የእረኝነት ተግባር ይወጡ ዘንድ ነው። ካህናት አባግዐ ክርስቶስ ምእመናንን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን እንዲያሰማሩ ሲሾሙ የተሰጧቸው አደራዎች (የተጣሉባቸው ግዴታዎች)፣ ይህንን ግዴታ ለመፈጸም የተሰጣቸው ሥልጣን ከተጠያቂነት ጋር እንደሆን በቅዱሳት መጻሕፍት ተዘርዝሯል። እነዚህን ከዚህ በታች በጥቂቱ ለመመልከት እንሞክር።
የካህናት ሥልጣን
በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ አንጻር ለካህናት የተሰጠው ሰማያዊ ስልጣን “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” (ማቴ ፲፮᎓፲፱፣ ማቴ ፲፰᎓፲፰) እንዲሁም “ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል።” (ዮሐ ፳፣፳፫) የሚል ጽኑ ሥልጣን ነው። ይህን የመሰለ ከምድር እስከ ሰማይ የሚዘልቅ ሥልጣን የትኛውም ምድራዊ ኃይል የለውም። እያንዳንዱ ካህን የዚህ ሥልጣን ባለቤት መሆኑ የሚያስገርምና የሚያስፈራም ነው። አስገራሚነቱ እግዚአብሔር ሥጋ ለባሽ ለሆነ እና ለራሱ እንኳ ከሥጋ ፍቃድና ከኃጢኣት ጋር ገና እየታገለ ለሚኖር ለደካማው የሰው ልጅ ይህን ያህል ሥልጣን መሰጠቱ ሲሆን አስፈሪነቱ ደግሞ ይህ ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር የተሰጠ መሆኑን ስንረዳ ነው።
የካህናት ኃላፊነት
ካህናት ዐርዓያ ክህነት ያላቸው፤በእወቀት የተካኑ፣በስነ ልቦና ዝግጁ የሆኑ፣ ከእግዚአብሐር ጋር ያላቸው ግንኙነት ያልተቋረጠ፣ በመንፈስ የጎለመሱ፣እግዚአብሔር የሰጣቸውን ኃላፊነት አክብረው የሚወጡ ሊሆኑ ይገባል፡፡
በሐዲስ ኪዳን ያሉ ካህናት ዋነኛ ኃላፊነት “ጠባቂነት” እንደሆነ ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ “ የዩና ልጅ ስምዖን ትወደኛለህን? “ በማለት ከጠየቀው በኋላ “ ግልገሎቼን ጠብቅ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሠማራ” በማለቱ ታውቋል። በትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕራፍ ፴፬ ላይ ስለእረኝነት የተነገረውን ቃል በሚገባ የሚያነብ ካህን የእረኝነት ኃላፊነትና ተግባር ምን መሆን እንዳለበት ይረዳል። እንኳንስ ሰማያዊ ሥልጣን የተሰጠው ካህን ህዝቡን የማስተዳደር ምድራዊ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው ምድራዊያን ነገሥታት በዚህ የመጽሐፍ ክፍል የተጠቀሱትን ኃላፊነቶች እንዳሉባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ።በዚህ የትንቢት መጽሐፍ የተጠቀሱትን የእረኞች ኃላፊነት አንጻር የሐዲስ ኪዳን ካህናት ኃላፊነት ምን እንደሆነ ለመመልከት እንሞክር።
ሀ) በጎችን በለመለመ መስክ ማሰማራት
የካህናት ተቀዳሚ ተልዕኮ ምእመናን ለምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሱታፌ ማብቃት ነው። ካህኑ ከምእመናን ልደት እስከ እረፍታቸው ድረስ በየደረጃው የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት በመስጠት በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት፣ በቅብዐ ሜሮን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ፣ ለአካለ መጠን ሲደርሱ በተክሊሉ የትዳር ህይወታቸውን በመባረክ፣ በኃጢኣት ሲወድቁ በንሰሐ ሳሙና በማጠብ፣ ሲታመሙ በጸሎተ ቀንዲል ፈውስን በመስጠት፣ በየጊዜው በጸሎተ ቅዳሴ በሚያቀርበው መስዋዕት ህዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ፣ ወተት የሆነ ቃሉን በመመገብ በክርስቲያናዊ ሕይወት በማጽናት ለሥጋ ወደሙ በማብቃት ለሰማያዊው ርስት ያዘጋጃቸዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ እያንዳንዱን በግ (ምእመን) በስም ማወቅና መለየት፣ ሳያሰልሱ መከታተል፣ ካለምንም ሌላ ተጨማሪ ጥቅም ሊቀርባቸውና ሊከታተላቸው፣ የሚመገቡትም ቃለ እግዚአብሔር እንክርዳድ ያልተቀላቀለበት ንጹሕ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ምክንያቱም የነፍስና የስጋ ጠባቂ ተደርጎ ተሾሟልና፡፡ ምእመናን “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል።” (መዝ ፳፪፡ ፩ -፪) ማለት የሚችሉትና የእግዚአብሔርን ቸርነት ሊረዱ የሚችሉት አዕይንተ እግዚአብሔር በተባሉ ካህናት በሚገባ ሲጠበቁና ቃሉን በአግባቡ ሲመገቡ ነው።
ለ) የደከመውን ማጽናት
በጎች ምእመናን በዚህ ዓለም ሃሳብና ውጣ ውረድ ሕሊናቸው ደክሞ፣ ሰውነታቸው ዝሎ ሕገ እግዚአብሔርን ሊዘነጉና ብሎም ወደ ክፋትና አምልኮ ጣዖት ሊሳቡ ይችላሉ፡ በዚህ ወቅት የካህኑ ተግባር በደከሙት መፍረድ ሳይሆን በቃለ እግዚአብሔር በማጽናት “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” (ማቴ ፲፩፡ ፳፰- ፴) የሚል አምላክ እንዳላቸው በማስታወስ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔርና ገቢረ ጽድቅ መመለስ ሊሆን ይገባል።
ሐ) የታመመውን ማከም
በጎች ምእመናን በደዌ ሥጋ በደዌ ነፍስ ሲጠቁ ካህኑ ሊለያቸው አይገባም። ደዌ ሥጋ ያገኛቸውን ልጆቹን በጸሎት፣ በጠበል ከመፈወስ ጀምሮ ለሥጋቸው በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሊከታተላቸው ይገባል። በ”ማይድን” ሥጋዊ በሽታ ተይዘው ለቀቢጸ ተስፋ የተዳረጉትን በቅርብ እየተገኘ በማጽናናት መንፈሳዊ ፈውስን የሚሰጥ አምላክ እንዳለ በማስተማር ማጽናናት እና ሰማያዊና ዘላለማዊ ሕይወት እንዳለ ማመላከት ይገባዋል። ከዚህም ሌላ በጎች ምእመናን በጥርጣሬ፣ በዓለማዊ ፍልስፍና፣ በኑፋቄ እና በክህደት ተይዘው ሊታመሙ ይችላሉ። በእነዚህ ደዌዎች የተያዙትንም በጎች ደዌ ሥጋ ከያዛቸው በበለጠ ጥንቃቄና በመንፈሳዊ ጥበብ “ማከም” ይገባል። ካህኑ ማንም ወዶና ፈቅዶ እንደማይታመም አውቆ በፍጹም ሀዘኔታ፣ በየዋሀት መንፈስና በመንፈሳዊ ጥበብ ከጾምና ጸሎት ጋር በደዌ ነፍስ የተያዙትን በጎች ማከም መቻል አለበት። ለካህኑ ዋጋ የሚያሰጠው የሳቱትንና የደከሙትን ተንከባክቦ ለንሰሓ ማብቃት እንጂ አውግዞ መለየት ሊሆን አይገባውም ምንም እንኳንበክህደት በኑፋቄ የታመሙትን መክሮ ዘክሮ የማይመለሱና ሌሎችን የማያስቱ ሆኖ ሲገኝ አውግዞ መለየቱ የግድ መሆኑ የማይቀር ቢሆንም “ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥ ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ” እንዲል። (ያዕ ፭፡ ፲፱_-፳)። ቅዱስ ይሁዳም በመልእክቱ “ አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።” (ይሁዳ ፳፪- ፳፫) በማለት የክርስቲያኖች በተለይም የካህናት ድርሻ በኑፋቄና በክህደት ትምህርት የተነጠቁትን ማዳን ጭምር መሆኑን አስገንዝቦናል።
መ) የተሰበረውን መጠገን
የምንኖርባት ዓለም በተለያዩ ተፈጠሮአዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያትን፣ በተጥባበ ሥጋ ብዛት፣ በሃይማኖት ባልተገራ ምድራዊ ፍልስፍና፣ በዘመናዊነት ስም በማኅበረሰቡ ላይ በተጫኑ አስጨናቂ የኑሮ ዘዬዎች ምክንያት… ወዘተ ከባለ ጸጋውም ከደሃውም ሕይወት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነው ደስታ የራቀበት በመሆኑ የብዙ ምእመናን ልብ በሐዘን የተሰበረ ነው። በመንፈሳዊ ሕይወት ለመጽናት የሚሞክሩትን ጭምር ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስጠነቀቀው ዲያብሎስ እንደሚያገሳ አንበሳ ዙሪያቸውን እየዞረ ያስጨንቃቸዋል “ በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” (፩ ጴጥ ፭፡ ፰፡) እንዲል። እነዚህን በሐዘን ወስጥ ያሉ እና በስነ ልቦና የተጎዱ ምእመናንን ካህኑ በመንፈሳዊ ጥበብና በቃለ እግዚአብሔር ማጽናት አለበት። ካህኑ በተለይም ልዩ ችግር ያለባቸውን ልጆቹን በመንከባከብ ከበጎቹ መካከል ሰባራዋን፣ አንካሳዋን ጠቦት በጥንቃቄና በቀስታ እንዲያሰማራ ሲያስፈልግም በእቅፉ የሚሸከማትን መልካም እረኛ ሊመስል ይገባል።
ሠ) የባዘነውን መመለስ
በቤተ ክርስቲያናችን በስፋት እንደሚታየው ብዙ ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸውን ባይተዉም ወደ ኑፋቄና ክህደት ባይገቡም ከሕገ እግዚአብሔርና ከምክረ ካህን ተለየተው በፍጹም ዓለማዊ ኑሮ ካላመኑት ባልተለየ ሕይወት እየተመላለሱ ይኖራሉ። ካህኑ ኃላፊነት ያለበት ለእነዚህ በአፍኣ ላሉ ምእመናን ጭምር በመሆኑ ወደ በረት/ ቤተ ክርስቲያን በመጡት ምእመናን ብዛት ሊዘነጋ አይገባውም። ካህናት ትኩረት ሊሰጡና በትጋት ሊሠሩበት የሚገባው ጉዳይ ይህ ነው ። የጸጋ ግምጃ ቤት ከሆነች ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው የዲያብሎስ መጫወቻ ለሆኑ ጥሙቃን ክርስቲያኖች ካህኑ ሊያዝንላቸው ይገባል።
ረ) የጠፋውን መፈለግ
ጌታችን በአንቀጸ አባግዕ ካስተማራቸው ትምህርቶች አንዱ “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምጼንም ይሰማሉ፥ አንድ መንጋም ይሆናሉ እረኛውም አንድ።” (ዮሐ ፲፡ ፲፮) ። ሕዝብና አህዛብን አንድ ያደረገ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ሥራውን የሠራው ዓለም ሁሉ በእርሱ እንዲያምንና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ነው። (ዮሐ ፫- ፲፮):: ስለሆነም ካህናት ለልጅነት ተጠርተው ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆኑ ያልተነገራቸውንየጠፉ የተባሉትን በማስተማርና በማጥመቅ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የመመለስ መንፈሳዊ ግዴታ አለባቸው። በተለይ ከሀገር ወጭ ያሉ ካህናት ተቀዳሚ ተግባራቸው ወንጌልን ላላመኑት ማድረስ በመሆኑሄዱበትን ሀገር ባህልና ቋንቋ መሳሪያ አድረገው ለማገልገል መዘጋጀት አለባቸው።
የምእመናን ድርሻ
ካህናት አባግዐ እግዚአብሔር ምእመናንን በመጠበቅ ረገድ ያለባቸው ኃላፊነት ከብዙ በጥቂቱ ከዚህ በላይ ተዘርዝሯል። ካህናቱ ይህን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ከተጠባቂዎቹ ምእመናንም የሚጠበቅ ነገር አለ። ካህናቱ የራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለማሟላት ከምእመናኑ ባልተናነሰ እየደከሙ ያለባቸውን የክህነት ኃላፊነት እንዲወጡ መጠበቅ አግባብ አይደለም። በመሆኑም ካህናቱ ተረጋግተው የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ምእመናን በኑሮአቸው ሊደግፏቸው ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ምእመናን በምክረ ካህን፣ በፍቃደ ካህን ለመኖር የወሰኑና ካህኑ በሚመራቸው መንገድ ለመጓዝ ፍቃደኛ መሆን አለባቸው እንጂ ለእረኝነት የሚያስቸግሩ ካህኑንም ሆነ ሌሎች ምእመናንን የሚያስቸግሩ እንዳይሆኑ እግዚአብሔር በቃሉ እንዲህ ሲል ይመክራል፤
“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ፥ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል፥ እፈርዳለሁ። የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል። እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ። እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥፤ ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ።” (ሕዝ. ፴፬: ፲፯- ፳፪) ይላልና ቃሉ ለእረኛችን ከተመቸኝ በለመለመ መስክ እናድራለን፡፡ከእረኛችን ከራቅንና ካልተመቸን በተኩላ /መናፍቅ/ዲቢሎስ እንበላለን፡፡

ማጠቃለያ
በምድራዊው አስተዳደር ባለሥልጣናት በተወሰነና በታወቀ የሕግ ገደብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ። በተሰጣቸው የሥልጣን ገደብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ከተወጡ ይመሰገናሉ። ይሸለማሉ። ያለበለዚያም ይወቀሳሉ፤ይከሰሳሉ። በጎች የተባሉ ምእመናን እንዲጠብቁ ሰማያዊ ሥልጣንን የተቀበሉ ካህናትም ከግል ሕይወታቸው በተጨማሪ በተሰጣቸው የክህነት ሥልጣን ምን እንደሰሩበት በሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ይጠየቃሉ። በመሆኑም ካህናት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለምእመናን ምሳሌና አርአያ በመሆን ከላይ የተዘረዘሩትን ኃላፊነቶች መወጣታቸውን በየጊዜው ራስቸውን መመርመር ይኖርባቸዋል። ምእመናንም ቸሩ እረኛ መድኃኔዓለም በዳግም ምጽኣቱ በቀኙ ከሚያቆማቸው በበጎች ከተመሰሉ ማኅበረ ጻድቃን ለመደመር በምክረ ካህን፣ በፍቃደ ካህን በመኖር ሕገ እግዚአብሔርን በመኖር ልንጸና ይገባል። ሁላችንም ኃላፊነታችንን በአግባቡ ተወጥተን የሰማያዊ ክብር ተካፋዮች እንድንሆን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን