በኒውዮርክና ኒውጀርሲ የሚገኙ አብያተ ክርስትያናት የአንድነት ጉባኤ አካሄዱ

በኒውዮርክና ኒውጀርሲ የሚገኙ አብያተ ክርስትያናት የአንድነት ጉባኤ አካሄዱ

ታላላቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ የሰላም እና የአንድነት ጉባኤ በሰሜን አሜሪካ ኒዋርክ ኒውጀርሲ ብስራተ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ጥቅምት ፫ ፳፻፲፩ ዓ.ም ተካሄደ። የኒውዮርክ ጽዮን ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ገዛኸኝ ፀሎተ ቅዳሴውን የመሩት ሲሆን ፣ የዕለቱ ትምህርተ ወንጌል “ምሕረትን እወዳለሁ’’ (ማቴ ፱፡፲፫) በሚል ርዕስ በመጋቤ ወንጌል ኤልያስ የብስራተ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ሰባኬ ወንጌል ተሰጥተዋል። በመቀጠል መልአከ ሰላም ዳኛቸው በእንግሊዝኛ ትምህርት የሰጡ ሲሆን ያለፈውን የመለያየት ዘመን ለቤተ ክርስትያን የጨለማ ጊዜ እንደነበረ አስታዉሰው ከዚህ በኋላ ግን ቤተ ክርስትያንን በአንድነት ማገልገል እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል። በዚህ ጉባኤ በ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ከሁለት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ አብያተ ክርስትያናት የመጡ ምዕመናን ተገኝተዋል።በዓሉን በተመለከተ ከሁሉም አብያተ ክርስትያናት የተውጣጡ ህፃናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች መዝሙር አቅርበዋል።

በመቀጠል የኒውዮርክ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስትያን አገልጋይ ርዕሰ መምህራን ብርሃኑ በዓሉን በተመለከተ የቅዱስ ያሬድ ወረቦችን አሰምተዋል። ምዕመናን በዕልልታ እና በጭብጨባ ከሊቃውንቱ እና ከመዘምራን ጋር አብሮ በመዘመር ለዚህ አንድነት ያበቃቸውን እግዚአብሔርን አመስግነዋል። ቅዳሴው፥ዝማሬው ልብን የሚመሰጥ ፣ መንፈስን የሚያድስ እና የሚያረጋጋ እጅግ በጣም ልዩ ነበር። ቀጥሎም የደስታ መግለጫ መልአከ ገነት ገዛኸኝ ያቀረቡ ሲሆን መለያየት ጥሩ ባይሆንም ቤተ ክርስትያን እንድትሰፋ ምክንያት ሁኗል ብለዋል። ከዚህ በኋላ ግን ቤተ ክርስትያንን በአንድነት በማገልገል እንደ መስቀል እና ጥምቀት ያሉ ዓበይት በዓላትን በጋራ ማክበር እንደሚገባ መክረዋል።ርዕሰ መምህራን ብርሃኑ ተመሳሳይ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን መወድስ ቅኔ በግዕዝ እና በአማርኛ ቀርቧል። በተለይ የሴራክዮስ ገነተ ደናግል ቅድስት አርሴማ ወክርስቶስ ሠምራ ገዳም አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ገነት ካሳሁን እንባ እየተናነቃቸው ያስተላለፉት መልእክት የብዙዎችን ልብ የነካ ነበር። ቤተ ክርስትያን  የማሕበረሰብ (Community) አገልግሎት ሳይሆን ምዕመናንን ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለው ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት የሚዘጋጁባት ቤተ መቅደስ መሆን እንዳለባት እና በተለይም ተተኪ ትውልድ ላይ በእጅጉ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል። በመጨረሻም ሰርሆተ ሕዝብ ከሆነ በኋላ በብስራተ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን አዳራሽ ጉባኤው ቀጥሎ ውሏል።

ምዕመናን አስቀድመው ቦታቸውን የያዙ ሲሆን አባቶች ካህናት ሲገቡ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በመዝሙር ፣ በዕልልታ እና በጭብጨባ በመቀበል ለአባቶች ካህናት ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል።በተጨማሪ ዲያቆን ዘካርያስ እና ዘማሪ መንግስቱ ወቅቱን የተመለከቱ መዝሙራትን በማቅረብ በዓሉን አድምቀውታል።  በዚሁ ጉባኤ በUN የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ ተገኝተዋል። የአዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ወንድም አገኘሁ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። አክለውም ይህንን የአባቶች አንድነት እንዲመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አመስግነዋል። በመቀጠል ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ ሲሆኑ የምስጋና መልዕክቱ በአግባቡና በስርዓቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንደሚያስተላልፉ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም ቤተ ክርስትያን ለአገር አንድነትና ሰላም ያደረገችው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። በመቀጠል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ተወካይ ወጣት መኮንን ቤተ ክርስትያን አፍሪካን አሜሪካን (African American) በእንግሊዝኛ ቋንቋ በማስተማር እንድትደርስላቸው ተማፅነዋል። ከዚህ በኋላ የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች መዝሙር በእንግሊዝኛ፤በግዕዝ፤በአማርኛ አቅርበዋል።

በተጨማሪ የኒውዮርክ ደብረ ብርሃን ቅድስት ስላሴ (በሰሜን አሜሪካ የመጀመርያው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ) አስተዳዳሪ መጋቤ አእላፍ ኤፍሬም የደስታ መግለጫ መልእክት አስተላልፈዋል። በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች የቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪ አባቶች ካህናት የተሰማቸውን የደስታ መግለጫ  መልእክት አቅርበዋል።ቀጥሎም በሰሜን አሜሪካ የማህበረ ቅዱሳን የኒውዮርክ ግንኙነት ጣብያ ሰብሳቢ ዲያቆን ዶክተር ምሕረተአብ “ዕርቅ የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና“ (ማቴ ፭፥፱) በሚል መነሻ ርዕስ ማህበሩ በአባቶች አንድነት የተሰማውን ደስታ ገልፀዋል። የማህበሩ አባላትም ልጆችን በማስተማር እና መዝሙራትን በማቕረብ ተሳትፈዋል። በመጨረሻም የአዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ወንድም አገኘሁ ይህንን ጉባኤ ያዘጋጁ ከ ፲፩ አብያተ ክርስትያናት የተውጣጡና ከማህበረ ቅዱሳን የተወከሉ ፪ አባላት በድምሩ ፳፬ አባላት እና በአጠቃላይ ይህንን ጉባኤ እንዲሳካ ለደከሙት ሁሉ ምስጋና በማቅረብ በአባቶች ካህናት ጸሎትና ቡራኬ የጉባኤው ፍጻሜ ሁኗል።